በኮሮና ቫይረስ ከተያዙ ሰዎች መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት በአነስተኛ የኢንፌክሽን ደረጃ ላይ ይገኛሉ

35
የካቲት 10/2012( ኢዜአ) በኮሮና ቫይረስ ከተያዙ ሰዎች መካከል 80 ነጥብ 9 በመቶ የሚሆኑት አነስተኛ በሆነ የኢንፌክሽን ደረጃ ላይ መሆናቸውን ጥናት አመለከተ። የቻይና የጤና ዘርፍ ሀላፊዎች የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ላይ የመጀመሪያውን ስፋትና ጥልቀት ያለው ጥናት ይፋ ማድረጋቸውን ቢ ቢ ሲ ዘግቧል። ጥናቱ ከ70 ሺህ በላይ ሰዎችን ያካተተ መሆኑም ተመልክቷል።
በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች መካከል 80 ነጥብ 9 በመቶ የሚሆኑት አነስተኛ የኢንፌክሽን ደረጃ፣ 13 ነጥብ 8 በመቶ የሚሆኑት በከባድ ደረጃ እንዲሁም 4 ነጥብ 7 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በአደገኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ተጠቁሟል። ዕድሜያቸው የገፉ እና ህመም ላይ ያሉ ሰዎች ለኮሮና ቫይረስ ተጋላጭነታቸው ከፍ ማለቱንና የወንዶች የሞት መጠን ከሴቶች ከፍ ያለ መሆኑንም ጥናቱ አመልክቷል። በቫይረሱ ህይወታቸው ካለፉት መካከል ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑ ዕድሜያቸው የገፉ እና ህመም ላይ ያሉ ሰዎች መሆናቸውን ከቻይና በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ከሟቾቹ መካከልም ዕድሜያቸው 80ና ከዛ በላይ የሚሆኑት ከፍተኛውን ድርሻ የያዙ መሆኑንና እስከ 39 ዓመት ዕድሜ ውስጥ የሚገኙት የሞቾች ቁጥር 0 ነጥብ 2 እንደሆነ ተገልጿል። የልብ ህመም ፣የስኳር ህመም ፣ ከባድ የመተንፈሻ አካላት ህመምና የደም ግፊት ያለባቸው ሰዎች ለቫይረሱ የበለጠ ተጋላጭ መሆናቸውም እንዲሁ። የህክምና ባለሙያዎች ለቫይረሱ ተጋላጭነታቸው ከፍ ያለ ሲሆን 1 ሺህ 716 የጤና ባለሙያዎች በቫይረሱ መያዛቸው መረጋገጡንና የአምስት ባለሙያዎች ህይወት ማለፉም በጥናቱ ተጠቅሷል። እ.ኤ.አ ከየካቲት 11/2020 ጀምሮ የቫይረሱ ምልክት የሚታይባቸው ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱም ተመልክቷል። ይህም ውጤት የተገኘው ቻይና የቫይረሱ ስርጭት የተስፋፋበት የውሃን ከተማና ሌሎች የሁቤ ግዛት አካባቢዎች ዝግ እንዲሆኑ ማድረጓና በአገሪቱ የጉዞ እገዳዎች መደረጋቸው በዋናነት በምክንያትነት ተጠቅሰዋል። የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የሚያስችሉ ትምህርቶች በመገናኛ ብዙሃን ተቋማት መሰራጨታቸው ፣ ስርጭቱን ለመግታት ዘርፈ ብዙ ስራዎች መሰራታቸውና ፈጣን ምላሽ መሰጠቱም ለተገኘው ውጤት አስተዋጽኦ ማድረጋቸው ጥናቱ ያሳያል። ሆኖም በርካታ ሰዎች ከአመት በዓል ዕረፍታቸው ወደ ቻይና እየተመለሱ በመሆኑ ስርጭቱ እንዳያገረሽ አገሪቷ ዝግጁ መሆን እንደሚኖርባት ጥናቱ አመልክቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም