የተጀመረው የብልጽግና ጉዞ እንዲሳካ የድርሻችንን እንወጣለን... የጎባ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች

85

ጎባ፤ የካቲት 10/2012 (ኢዜአ) በመንግስት የተጀመረው የአንድነት፣ የፍቅርና የለውጥ ጉዞ ከዳር እንዲደርስ ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ በባሌ ዞን የጎባ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ።

ነዋሪዎቹ የለውጥ እንቅስቃሴዎችን በመደገፍ ዛሬ በጎባ ከተማ ሰልፍ አካሒደዋል።

"የብሔር ብሔረሰቦችን አንድነት በማጠናከር የአካባቢያችንን ሰላም እናረጋግጣለን"፣ "ለውጥን እንደግፍ ዴሞክራሲን እናበረታታ" የሚሉና ሌሎች መልዕክት የተላለፈበት የድጋፍ ሰልፉ ከከተማ አስተዳደሩና አካባቢው የተወጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈውበታል።

ከተሳታፊዎች መካከል አቶ ከተማ በየና እንደገለጹት እስከአሁን በሀገሪቱ የመጡትን ለውጦች በመደገፍና በማበረታታት በቀጣይም ከመንግስት ጎን ለመቆም ዝግጁ ናቸው።

አሁን እየተመዘገቡ በሚገኙ ለውጦች ደስተኛ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ከተማ ለዘመናት አብሮ የኖረውን ህዝብ ለመከፋፈል የሚጥሩ ቡድኖችን አጥብቀው እንደሚያወግዙ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሰላም፣ ለፍቅርና ለአንድነት የሰጡት ዋጋና የመጣው ለውጥ ለድጋፍ እንዲወጣ ያነሳሳው መሆኑን የገለጸው ደግሞ ሌላው የሰልፉ ተሳታፊ ወጣት አብረሃም በየነ ነው።

"ለህዝቦች ነፃነትና ለእውነት የቆሙ አንድነትን ያረጋገጡ የኢትዮጵያ መሪ መሆናቸውን በአጭር ጊዜ ውስጥ በተግባር ባከናወኗቸው ሥራዎችና ባመጧቸው ለውጦች አረጋግጠናል" ብሏል።

አቶ ጥለሁን መንግስቱ በበኩላቸው "ዛሬ በድጋፍ ሰልፉ ላይ ስንሳተፍ ከምስጋና ባለፈ የጠቅላይ ሚኒስትሩን መርህ ተከትለን ያሰቡት እንዲሳካ ከጎናቸው መቆማችንን በተግባር ለመግለጽ ጭምር ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

በድጋፍ ሰልፉ ላይ የተገኙት የጎባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ንጋቱ ሞቱማ በበኩላቸው፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ እየተመዘገቡ ያሉ ለውጦች አበረታች ናቸው ብለዋል።

ነዋሪዎችም አገራዊ ለውጦቹ ከዳር እንዲደርሱ ከመንግስት ጎን በመቆም የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

የባሌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ዲዳ ጉደታ እንደተናገሩት የተጀመሩ ሀገራዊና ክልላዊ ለውጦች ከዳር እንዲደርሱ ሁሉም የዞኑ ነዋሪዎች በአንድነት ሊቆሙ ይገባል።

ለልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠትም አስተዳደራቸው በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸው፤ በተለይ ወጣቶች በልማቱ ተሳታፊ በመሆን ራሳቸውንና ሀገራቸውን መለወጥ እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።

በድጋፍ ሰልፉ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያመጧቸውን ለውጦች የሚያበረታቱና ለለመጡ እውቅና የሚሰጡ መልዕክቶች ተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም