ድጋፍ በማጣት የስራ እድል ተጠቃሚ መሆን እንዳልቻሉ በጎንደር ተመራቂ ወጣቶች ተናገሩ

153

ጎንደር፣ጥር 10/2012 (ኢዜአ) በማህበር ተደራጅተው የስራ እድል ተጠቃሚ ለመሆን ቢፈልጉም ድጋፍ በማጣት እንዳልቻሉ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው በጎንደር ከተማ የሚገኙ ወጣቶች ተናገሩ፡፡

የከተማ አስተዳደሩ በበኩሉ ወጣቶቹን ወደ ስራ ለማስገባት ያጋጠመውን የቦታና የብድር አቅርቦት ችግር ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጿል።

ከሃዋሳ ዩንቨርሲቲ በሲቪል ምህንድስና የተመረቀው ወጣት ዳንዔል ፍፁም እንዳለው በግንባታ ዘርፍ የስራ እድል ተጠቃሚ ለመሆን ተመሳሳይ ሙያ ካላቸው ጓደኞቹ ጋር ቢደራጅም ወደ ስራ መግባት ግን አልቻለም።

የከተማ አስተዳደሩ ሲያደራጃቸው በግንባታ ስራዎች ተሳታፊ ትሆናላችሁ በማለት ቃል ቢገባም ስራ ሳያገኙ ከአንድ ዓመት በላይ እንደሆናቸው ተናግሯል።

ከደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በባዮሎጂ የተመረቀው ወጣት ነጋ አባተ በበኩሉ በዳቦ ማምረት የስራ ዘርፍ ለመሰማራት ከ12 ጓደኞቹ ጋር  ቢደራጁም የመስሪያ ብድር ማግኘት ባለመቻላቸው ወደ ስራ መግባት እንዳልቻሉ ገልጿል።

“በከተማ ግብርና ዘርፍ ለመሰማራት 16 ሆነን ከተደራጀን ከሁለት ዓመት በላይ ሆኖናል” ያለችው ደግሞ ከሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ በተፈጥሮ ሀብት የተመረቀችው ወጣት ራሄል አዛዡ ናት፡፡

ወጣቷ እንዳመለከተችው በከተማ አስተዳደሩ እንደ ችግር እየተነሳ የሚገኘው የብድርና የቦታ አቅርቦት እጥረት ቢሆንም ካለባቸው ችግርና የኑሮ ጫና አንጻር አግባብ አይደለም።

በከተማ አስተዳደሩ ቴክኒክና ሙያ ኢንተርፕራይዞች ልማት መምሪያ የስራ እድል ፈጠራ ቡድን መሪ አቶ ዮሴፍ ሞላ እንደገለጹት ወጣቶቹ በተደራጁበት ቅደም ተከተል ወደ ስራ እንዲገቡ እየተደረገ ነው።

ሆኖም በከተማዋ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ መዳከም፣ የብድርና የቦታ አቅርቦት ችግር በማጋጠሙ የተደራጁ ወጣቶችን በሙሉ ወደ ስራ ለማስገባት አልተቻለም፡፡

በከተማዋ 81 የተደራጁ ማህበራት ቢኖርም በበጀት ዓመቱ እስካሁን 22 ማህበራትን ብቻ ወደ ስራ ማስገባት መቻሉን ጠቁመው የዘገየውም ለነባሮቹ ትኩረት በመስጠት እንደሆነ አስረድተዋል።

ቡድን መሪው እንዳሉት በተለይም የብድር አቅርቦት ችግር እየተከሰተ ያለው በተዘዋዋሪ ፈንድ የተሰራጨው 87 ሚሊየን ብር ብድር  አመላለስ 25 በመቶ ብቻ በመሆኑ የተከሰተ ችግር ነው።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ተሾመ አግማስ በበኩላቸው የተደራጁ ወጣቶችን ወደ ስራ ለማስገባት የሚያስችል የኢንቨስትመንት ዘርፉን ለማሳደግና ባለሃብቱን ለመሳብ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም የተዘዋዋሪ ብድር ወስደው ያልመለሱ ወጣቶች በየክፍለ ከተማው አጥርቶ በማስመለስ ለሌሎች ወጣቶች ለማሰራጨት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በከተማው የስራ እድል ተጠቃሚ ለመሆን በተለያዩ ማህበራት የተደራጁ ከ5ሺህ 150 በላይ ወጣቶች ቢኖሩም ወደ ስራ የገቡት ከአንድ ሺህ 300 በታች መሆናቸውን መምሪያው አመልክቷል።