በሰሜን ሽዋ ዞን መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ህዝብን የሚጠቅም የልማት ሥራዎችን እያከናወኑ ነው

78
ደብረ ብርሃን ሚያዝያ 25/2010 በአማራ ክልል ሰሜን ሽዋ ዞን የሚንቀሳቀሱ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ተግባራትን በማከናወን ላይ መሆናቸውን የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ ገለፁ። መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር የ2018 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ለመገምገም የሚያስችል የምክክር መድረክ በዓለም ከተማ ተካሄዷል። ምክትል አስተዳዳሪው አቶ ታደሰ ገብረጽዮን በምክክር መድረኩ ላይ እንዳሉት መንግስት በልማት ሥራ ያልሸፈናቸውን ቦታዎች መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በመሸፈን ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ በማድረግ የድርሻቸውን እየተወጡ ይገኛሉ፡፡ "ድርጅቶቹ በተለይ በንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ በእናቶችና ሕጻናት፣ በትምህርት፣ በአቅም ግንባታና በሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች በመሳተፍ ለሕብረተሰቡ የሚሰጡት እገዛ የሚበረታታ ነው" ብለዋል። መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በገቡት ውል መሰረት እየሰሩ ስለመሆናቸውና በአሰራራቸው ላይ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን አቶ ታደሰ ጠቁመው፣ በዚህም አብዛኞቹ ድርጅቶች በውላቸው መሰረት እየሰሩ ስለመሆናቸው መታወቁን ተናግረዋል። ሁለት መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የገቡትን ውል መፈጸም ባለመቻላቸው ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸውም አስረድተዋል። በዞኑ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት መምሪያ የመንግስት ትብብር ባለሙያ አቶ ጌቱ መንግስት በበኩላቸው፣ በዞኑ በዚህ ዓመት ብቻ 44 መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች 85 የልማት ፕሮጀክቶችን በማከናወን ላይ ይገኛሉ። ለነዚህ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያም ድርጅቶቹ 186 ሚሊዮን ብር በጀት መድበው ወደስራ መግባታቸውንም አመልክተዋል። በተደረገው ድጋፍና ክተትል አሰራራቸው ግልጽነት የጎደለው፣ አሳማኝ ሪፖርት የማያቀረቡ፣ ለኪራይ ሰብሳቢነት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር የጨረታ ሂደት የሚጠቀሙ ድርጅቶች እንዳሉ መታወቁን ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪ ከመንግስት ጋር በተዋዋሉት መሰረት የማይፈጽሙ፣ ህግና ደንቡን የማይጠበቁ እንዲሁም ፕሮጀክቶችን የሚያጓትቱ መንግስታዊ ያልሆን ድርጅቶች መስተዋላቸውንም ጠቁመዋል። "የአፈጻጸም ድክመት ያለባቸው ድርጅቶችም ከችግራቸው እንዲቆጠቡ ተቀራርቦ በመስራት እገዛ እየተደረገላቸው ይገኛል" ብለዋል። የ"ጀዊሽ ቮይስ ሚኒስትሪስ ኢንተርናሽናል ድርጅት" አስተባባሪ ዶክተር ኪዳነ በራሶ በበኩላቸው ስራቸውን ለማቀላጠፍ ከዞን እስከ ወረዳ ያሉ ባለሙያዎች ድጋፍ ሊለያቸው እንደማይገባ ነው የገለጹት። በሩብ ዓመቱ ለደብረብርሃንና አካባቢው ነዋሪዎች በተለያዩ የሕክምና ዘርፎች ለ16 ሺህ 598 ሰዎች አገልግሎት መስጠታቸውን ተናግረዋል። በኢንተርናሽናል ፈንድ አፍሪካ በጎ አድራጎት ድርጅት የፕሮግራሞች ዳይሬክተር ወይዘሮ ጸዳይ በዛብህ በበኩላቸው ''በተለያዩ የዞኑ ወረዳዎች ተዘዋውሮ ለመስራት የመንገድና የውሃ እጥረት ጫና ፈጥሮብናል'' ብለዋል። የውይይት መድረኩ በተስተዋሉ ችግሮች ላይ  መፍትሄ ለመስጠት ከማገዝ በላይ ከመንግስት ተቋማት ጋር የበለጠ ተቀራርቦ ለመስራት ዕድል እንደሚሰጣቸው ተናግራዋል። በምክክር መድረኩ ላይ የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅት ተወካዮችና ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ መሆናቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም