የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ቁጥጥሩ ተጠናክሮ ቀጥሏል

134

አዲስ አበባ ፤ የካቲት 10/2012 (ኢዜአ) የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19)ን ለመከላከል እየተደረገ ያለው ቁጥጥርና ክትትል በተጠናከረ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አሰታወቀ።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በቫይረሱ ተጠርጥሮ በለይቶ ማቆያ ማዕከል ያለ ሰው አለመኖሩም ተገልጿል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ በአገር አቀፍ ደረጃ ቫይረሱን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን በሚመለከት ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በኢትዮጵያ አየር መንገድና በአገሪቱ ባሉ 27 ኮሪደሮች/መግቢያ በሮች ላይ እየተከናወነ ያለው የቁጥጥርና የክትትል ስራ በተሳካ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ከጥር 15 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በ7ቱ መግቢያዎች ከ146 ሺህ 357 በላይ መንገደኞች በሙቀት ልየታው ያለፉ ሲሆን ከነዚህ ውስጥም 3 ሺህ 901 ቫይረሱ መኖሩን ሪፖርተ ካደረጉ አገራት የመጡ ናቸው።

በአጠቃላይ በሁሉም ወደ አገር መግቢያ ጣቢያዎች 248 ሺህ 734 ዜጎች በሙቀት መለያው እንዳለፉና 697 የሚሆኑት ደግሞ ባሉበት ቦታ ሆነው የጤና ክትትል እየተደረገላቸው ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ እስካሁን በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተጠቃ ሰው የለም ብለዋል።

እስካሁን 60 የጥርጣሬ መረጃዎች ለኢንስቲትዩቱ የድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ ማስተባበሪያ ማዕከል ደርሶ እንደነበር አስታውሰው በሁሉም ጥቆማዎች ላይ የማጣራትና የቁጥጥር ስራ ተከናውኗል ብለዋል።

ከጥቆማዎቹ መካከል 17ቱ በቫይረሱ ተጠርጥረው ስለነበርና የቻይና የጉዞ ታሪክ ስለነበራቸው በተለያየ ግዜ በለይቶ ማቆያ ማዕከል እንዲቆዩ ተደርጓል።

በተደረገላቸው የላብራቶሪ ምርመራ ውጤታቸው ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸው ተረጋግጦ ወደ ሕብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ ተደርጓልም ነው ያሉት።

በተጨማሪም በቀጣይ ሊኖሩ የሚችሉ ተጠርጣሪዎች በለይቶ ማቆያ ማዕከል ክትትል ለማድረግ የካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታል ውስጥ የተዘጋጀው ማዕከል ዝግጁ መሆኑንም አክለዋል።

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ የኢንስቲትዩቱ የድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ ማስተባበሪያ ማዕከል ሙያተኞችና ላብራቶሪው ለ24 ሰአት ዝግጁ ሆነው በመስራት ላይ ይገኛሉ።

በነጻ የስልክ መስመር 8335 ላይም የሕብረተሰቡ ጥቆማና መረጃ በተጠናከረ ሁኔታ መስጠቱ እንደቀጠለ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለያዩ ማህበራዊ ድህረ ገዖች ከቻይና የሚመጡ መንገደኞች ምንም አይነት የሙቀት ልየታ ምርመራ ሳይደረግላቸው እየገቡ ነው የሚለው መረጃም ስህተት መሆኑንም አስረድተዋለ።

ኢንስቲትዩቱ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመተባበር መንገደኞችን የመቆጣጠርና የመከታተል ስራውን በቅንጅት እየተሰራም እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በዓለም የጤና ድርጅት ሪፖርት መሰረት ከጥር 15 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ  እስከ የካቲት 10 ቀን 2012 ዓ.ም  ድረስ 71 ሺህ 432 ዜጎች በኮቪድ-19 ተይዘዋል።

1 ሺህ 775 ሰዎች ደግሞ በዚሁ ቫይረስ ሳቢያ ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን፤ በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ በግብጽ አንድ ሰው በቫይረሱ መያዙም ተረጋግጧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም