ዶክተር ፈንታ ማንደፍሮ የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ሆነው ተሾሙ

55
ባህር ዳር  የካቲት  10/202 (ኢዜአ) ዶክተር ፈንታ ማንደፍሮ የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ሆነው ተሾሙ፡፡ በባህርዳር እየተካሄደ ላለው  የክልሉ ምክር ቤት አስቸኳይ ጉባኤ  ዶክተር ፈንታን በእጩነት ያቀረቡት ርዕሰ መስተዳደር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ናቸው። ርዕሰ መስተዳደሩ እንዳሉት ዶክተር ፈንታ የተሻለ የትምህርት ዝግጅትና በአመራርም ሆነ በሙያ ሰፊ ልምድ ያላቸው ናቸው። በእጩነት ሲያቀርባቸውም ካላቸው ልምድና እውቀትም አሁን በክልሉ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማምጣት እንደሚችሉ አምነውባቸው እንደሆነ አመልክተዋል። የመንግስት ስራ የተቃና እንዲሆንና የተሻለ አፈፃፀም እንዲመጣ የካበተ ልምድም ሆነ እውቀት ያላቸው በመሆኑ የምክር ቤቱ ጉባኤ እንዲያጸድቅላቸው ጠይቀዋል። በክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ተመስገን ጥሩነህ የቀረቡትን የዶክተር ፈንታ ሹመት የምክር ቤቱ ጉባኤ ተቀብሎ በአብላጫ ድምጽ አፅድቋል። በዚህም 136 ድምጽ በድጋፍ ፣ 44 በታዕቅቦና ሦስት ደግሞ በተቃውሞ ሆኖ ሹመታቸው በአብላጫ መጽደቁ ታውቋል። በክልሉ ከዚህ በፊት ምክትል ርዕሰ መስተዳደር የነበሩት አቶ ላቀ አያሌው  የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ እና አቶ ዮሐንስ ቧያለው በፌደራል ደረጃ የተሾሙ መሆናቸውን አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገልፀዋል። እንዲሁም በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ መላኩ አለበልና የከተማ ልማትና ቤቶች ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃለፊ አቶ ፈንታ ደጀን በፌደራል መንግስት ኃላፊነት የተሰጣቸው በመሆኑ በምትካቸው ሌሎች እጩዎች እንደሚቀርቡም አቶ ተመስገን አስታውቀዋል። በምክር ቤት አባል የነበሩ አመራሮች ከክልሉ ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር መነሳት እንደሌለባቸው ከጉባኤተኛው አስተያየት ተሰጥቷል። በአሁኑ ወቅትም ለክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንትነት አቶ አብየ ካሳውና አቶ ኃይለየሱስ ተስፋማርያም በእጩነት ቀርበው ውይይት እየተደረገ ይገኛል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም