ኢትዮጵያ የማንኛውም አገር ዜጋ ሊጎበኛትና ታሪኳን ሊጋራ የሚገባ አገር ናት - የአፍሪካ ባህላዊ መሪዎች

55

አዲስ አበባ የካቲት 10/2012 ( ኢዜአ) ኢትዮጵያ የማንኛውም አገር ዜጋ ሊጎበኛትና ታሪኳን ሊጋራ የሚገባ አገር ናት ሲሉ የአፍሪካ ባህላዊ መሪዎች ተናገሩ።

ኢትዮጵያ ለበርካታ ዘመናት የዘለቀ የታሪክ፣ የባህል፣ የቋንቋና የሃይማኖት እሴቶች ያሏት አገር ናት።

በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) ያስመዘገበቻቸው 13 ቅርሶችም አሏት።

ከተመዘገቡት ቅርሶች መካከልም 9 የሚዳሰሱ ሲሆኑ 4 የማይዳሰሱ ናቸው።

በዚህም ከአፍሪካ በርካታ ቅርሶችን በዩኔስኮ ማስመዝገብ የቻለች ቀዳሚ አገር መሆኗን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

እነዚህን የዓለም ቅርሶችና ሃብቶች ለመመልከትም ከአለም አገራት በርካታ ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ በየዓመቱ ይጎርፋሉ።

ባለፈው አመትም የካሜሮንና የአይቮሪኮስት ንጉሳውያን መሪዎችም የኢትዮጵያን ታሪካዊ ስፍራዎችና ቅርሶች ከጎበኙት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።

የካሜሮን ንጉስ ዶክተር ሮቢንሰን ታኒዬ ኢትዮጵያ ትልቅ የቱሪዝም ኢንደስትሪ ያላት ድንቅ አገር መሆኗን ይገልጻሉ።

ከጎበኟቸው መካከል የአክሱም ሃውልትና ሌሎችም እጅግ ማራኪና የሚያስደንቅ የዓለም ቅርስ መሆናቸውን ገልፀው ኢትዮጵያ ታሪክና ቅርሷን ይበልጥ ለመጠቀም የቱሪስት መስህቦቿን ማልማት ይገባታል ብለዋል።

ንጉሱ አክለውም የሚኒልክን መኖሪያ ቤትና አሁን ወደ ቱሪስት መስህብ የተቀየረውን የመንግስት ቤት መጎብኘታቸውንም ገልጸዋል።

ይህም የአፍሪካ ባህልና ወግ ማከማቻ ሲሆን የቱሪስት መስህቦቹም የህዝቦች ወግና ባህል እንዲያቆጠቁጥ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።

የአይቮሪኮስት ንጉስ ዶክተር ቺፊዚ ጀንደርቫ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የታሪክ ሁሉ መነሻና የሰው ዘር መገኛ አገር መሆኗን ዓለም ሁሉ በአግባቡ ሊረዳው እንደሚገባ ይናገራሉ።

ኢትዮጵያ የሃይማኖት ብዝሃነትና ጥልቅ እምነት ያለባት አገር መሆኗንም እንዲሁ።

በመሆኑም የባህልና የሃይማኖት መነሻ አገር በመሆኗ የሁሉም አገር ዜጋ ኢትዮጵያን ሊጎበኛትና ታሪኳንም በቅጡ ሊያውቅ ይገባል ባይ ናቸው።

ኢትዮጵያ የሁሉ መገኛ (Land of Origins) በሚል ብራንድ ባህሏን፣ ቅርሶቿንና አጠቃላይ ታሪኳን ለዓለም በማስተዋወቅ ላይ ትገኛለች።

በ2020 በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በሚካሄደው የዓለም ኤክስፖ ላይም በዚሁ መሪ ሃሳብ ለዓለም ለማስተዋወቅ ዝግጅት በመደረግ ላይ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም