በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው የደም ልገሳ ባህል እየተሻሻለ መምጣቱ ተገለጸ

84

አዲስ አበባ የካቲት 9/2012 (ኢዜአ) በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው የደም ልገሳ ባህል እየተሻሻለ መምጣቱን የብሄራዊ ደም ባንክ የጤና ባለሙያ ተናግረዋል። የብሄራዊ ደም ባንክ በተቋማትና በተለያዩ ስፍራዎች በመገኘትና ህብረተሰቡን በመቀስቀስ የደም እጥረት እንዳይኖር እየሰራ ይገኛል።

የደም ባንክ ከተቋቋመ ጀምሮ በደም አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ለውጥ መምጣቱንም በብሄራዊ ደም ባንክ የጤና ባለሙያ የሆኑት አቶ ሙላት በቀለ ተናግረዋል፡፡

ለዚህም እንደ አብነት የሚጠቀሰው ቀደም ብሎ በቤተሰብ ምትክ ደም እየተሰጠ የሚገኘው አገልግሎት በአሁኑ ወቅት በበጎ ፈቃድ ደም ለጋሾች በሚገኘው ደም በመታገዝ ያለምትክ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ ግልጋሎቱ እየተሰጠ ይገኛል፡፡

በዚህም የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሰራተኞች ለሶስተኛ ጊዜ ዛሬ የደም ልገሳ አከናውነዋል።

በወቅቱ የደም ልገሳ ሲያደርጉ ያነጋገርናቸው የመስሪያ ቤቱ ባልደረባ አቶ አበበ ጌታሁን የደም ልገሳ ሲያደርጉ አምስተኛ ጊዜያቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ደም በመለገሳቸው የሰው ህይወት ማትረፍ መቻሉ እርካታ እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል።

የደም እጥረት ሲያጋጥም የደም ልገሳ አድርገው እንደሚያውቁ ጠቅሰው አሁን ደግሞ ችግሩ ሳይፈጠር ቀድመው ለወገን መድረሳቸውና ተቋማዊ በሆነ መንገድ ይሄንን ደም ልገሳ ማድረጋቸው እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።

የጤና ባለሙያው አቶ ሙላት በቀለ ተቋሙ በተለያዩ ቦታዎች ቅስቀሳ በማድረግና አንዳንድ ተቋማትም ጥሪ ሲያደርጉላቸው በቦታው በመገኘት ደም ለመለገስ መሟላት ያለባቸውን ቅድመ ሁኔታ በማሟላት የደም ልገሳውን እንደሚቀበሉ ገልጸዋል።

አሁን ላይ የህብረተሰቡ የደም ልገሳ ባህልም ከጊዜ ወደጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ጠቅሰው፤ በደም ዕጦት ምክንያት የሚሞቱ ዜጎችን ህይወት ለመታደግ ከዚህ በላይ መስራት እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

አንድ ሰው የደም ልገሳ ካደረገ ከሶስት ወር በኋላ በድጋሚ ደም ቢለግስ ምንም ችግር ስለማይፈጥር በደም ልገሳ ውስጥ ያሉ የተሳሳቱ አስተሳሰቦች መቀረፍ አለባቸው ሲሉ አሳስበዋል።

ሌላዋ ደም ለጋሽ የኢዜአ ባልደረባ ወይዘሪት ሰርካለም ተበጀ በበኩላቸው በደም እጥረት ምክንያት የሚሞቱ እናቶችን ህይወት ለመታደግ ደም በመለገስ የበኩላቸውን ሃላፊነት በመወጣታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አክለውም ሁሉም ተቋማት ይህንን ሰናይ ተሞክሮ ወደ ተቋማቸው በመውሰድና ሰራተኞቻቸውን በማስተባበር ደም የመለገስ ባህሉን እንዲያስፋፉ አሳስበዋል።

ባለፉት ዓመታት በጠቅላላው በህብረተሰቡ ዘንድ ደም የመለገስ ልምድና ባህሉ እየጎለበተ በመምጣቱ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች በአሁኑ  ወቅት በበጎ ፈቃድ ተነሳሽነት ደም በመለገስ ላይ ይገኛሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም