በከተሞች ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ታቅፈው እራሳቸውን የቻሉ የቤተሰብ አባላት ተመረቁ

41
ደሴ ኢዜአ የካቲት 9/2012 ፡- በደሴ በከተሞች የምግብ ዋስትና እና ስራ እድል ፈጠራ ፕሮግራም ታቅፈው በተደረገላቸው ድጋፍ እራሳቸውን የቻሉ ከ500 በላይ የቤተሰብ አባላት ተመረቁ። የደሴ ከተማ ምግብ ዋስትና እና ስራ እድል ፈጠራ ጽህፈት ቤት ኃለፊ አቶ ሐሰን ሙህዬ በምረቃው ስነስርዓት ወቅት እንደገለጹት እራሳቸው ችለው የተመረቁት ፕሮግራሙ ከተጀመረ ከ2009 ዓ.ም. ጀምሮ  ድጋፍ ሲደረግላቸው የቆዩ ዜጎች ናቸው፡፡ ድጋፍ ሲደርግላቸው የቆዩትም ተመራቂዎቹን ጨምሮ  ከ18 ሺህ በላይ በድህነት  ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች ናቸው። "ተመራቂዎቹ በተለያዩ የልማት ስራዎች በማሳተፍ የምግብ ዋስትና ክፍተታቸውን እንዲሞሉ በተደረገ ጥረት ፈጥነው ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት የቻሉ ናቸው" ብለዋል። በተለያዩ የገቢ ማስገኛ የልማት ዘርፎች በማሳተፍ ዘላቂ የገቢ ምንጭ እንዲፈጥሩ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል። ተጠቃሚዎቹ በፕሮግራሙ ታቅፈው በተደረገላቸው ድጋፍ እራሳቸውን የቻሉ 536 የቤተሰብ አባላት ትላንት ተመርቀዋል። እንደ ኃላፊው ገለጻ ተመራቂዎቹ በከተማ ጽዳትና ውበት፣ መሰረተ ልማት ግንባታ፣ በተፋሰስና ግብርና ስራዎች  ከማገልገላቸውም ባለፈ የስራ ባህላቸውን እንዲያዳብሩም ተደርጓል። እራሳቸውን የቻሉ  ሌሎች 6 ሺህ ዜጎች ደግሞ በዚህ ወር መጨረሻ  ተመርቀው የራሳቸውን የገቢ ማስገኛ ሥራ ይጀምራሉ፤ ቀሪዎቹ በሂደት ላይ ናቸው ተብሏል። ከተመራቂዎች መካከል የሰኞ ገበያ ከፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ ሀሰን መሃመድ በሰጡት አስተያየት ፕሮግራሙ የስራ ባህላቸውን ከማሳደጉም ባለፈ ከድህነት ወጥተው ኑሯቸውን እንዲያሻሻሉ እገዛ እንዳደረገላቸው ተናግረዋል፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት ተቸግረው የሰው እጅ አይተው ይኖሩ እንደነበር አስታውሰው፤ በተደረገላቸው ድጋፍ እራሳቸውን መቻላቸውን ገልጸዋል። ለአራት ቤተሰቦቻቸው በየወሩ አንድ ሺህ 200 ብር እየተከፈላቸው የልማት ስራዎችን ሲያከናወኑ መቆየታቸውና የስራ ባህላቸውም መቀየሩን ጠቅሰዋል። በተጨማሪም 420 ሆነው በማህበር ተደራጅተው በ60 ሄክታር ለምነቱ የተሟጠጠ መሬት እንዲያገግም በማድረግ አትክልትና ፍራፍሬዎችን እያለሙ በየወሩ ከ100 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘት መጀመራቸውን አሰረድተዋል። ማግኘት በጀመሩት ገቢም በጋራ  210 ሺህ ብር ከመቆጠባቸውም ባለፈ ማህበራዊ ኑሯቸውንም ማጠናከር እንደቻሉ ተናግረዋል። ወይዘሮ የትምወርቅ ዮሴፍ በበኩላቸው በቆይታቸው ያገኙትን የስራ ባህልና ድጋፍ በመጠቀም ተደራጅተው  በጦሳ ተራራ ላይ አትክልትና ፍራፍሬ እያለሙ በምግብ ራሳቸውን ከመቻላቸውም ባለፈ ኑሯቸውን እንዳሻሻሉ ገልጸዋል፡፡ ዘመናዊ የቤት ቁሳቁስ አሟልተው  ልጆቻቸውን በግል ትምህርት ቤት ጭምር ከፍለው ማስተማር እንደቻሉ ጠቅሰው፤ በቀጣይም በበግ እርባታ ለመሰማራት መዘጋጀታቸውን ጠቅሰዋል። በምረቃው ስነ ስርዓት የደሴ ክፍለ ከተሞች አመራሮችና የተመራቂ ቤተሰቦች ተገኝተዋል። የፕሮግራሙ አንዱ አካል የሆነና ከአንድ ሺህ በላይ የጎዳና ተዳዳሪዎችን የማንሳት ስራ ባለፈው ሳምንት መጀመሩም ኢዜአ  በወቅቱ ዘግቧል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም