ከ11 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ ፈጣን የሆነ የመልሶ ማልማት ሥራ ይፈልጋል

179
አዳማ (ኢዜአ) የካቲት 09/2012 በሀገሪቷ ከ11 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ ፈጣን የሆነ የመልሶ ማልማት ሥራ እንደሚፈልግ የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ገለጸ። ዓመታዊ የአካባቢና የደን ልማት የምርምር ሥራዎች ግምገማ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል። የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ከበደ ይማም እንደገለጹት በሀገሪቷ ከ53 ሚሊዮን ሄክታር በላይ የሚሆነው መሬት መከላቱን ገልጠዋል። ከዚህም ውስጥ 11 ሚሊዮን የሚሆነው ሄክታር አፋጣኝ የመልሶ ማልማት ሥራ የሚፈልግ ነው ያሉት አቶ ከበደ ይህን ማድረግ ካልቻን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ድርቅና በረሃማነት እንገባለን ብለዋል። የአካባቢና የደን ምርምር ኢንስቲትዩት ፈጥነው የሚደርሱ የደን ዝርያዎችን በምርምር በማውጣት የአረንጓዴ አሻራ ልማት ውስጥ ግንባር ቀደም ሚናውን መወጣት እንደሚገባው አስገዝበዋል። በተለይ የውጭና የሀገር በቀል ዛፎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት እንዲበቁ የመለየትሥራ፣በምርምር የተገኙ ውጤቶች ፈጥነው ወደ ህብረተሰቡ እንዲወርዱና ተግባራዊ እንዲሆኑ ሁላችንም የድርሻችን እንወጣለን ብለዋል። ባለፉት ዓመታት በሀገር አቀፍ ደረጃ በተከናወኑ የአፈርና ውሃ ዕቀባ ሥራ፣የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ የደን ሽፋናችን ከነበረበት 3 በመቶ ወደ 15 በመቶ ያደገ ቢሆንም አሁንም ከፍተኛ ቁርጠኝነትና ርብርብ የሚጠይቅ ሥራ ይጠበቅናል ነው ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ። በአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ የሚመጣውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ለመቋቋም የሚያስችል የደን ልማት ሥራዎች በሳይንሳዊ መንገድ ለማከናወን የሚያስችል ምርምር እያከናወን እንገኛለን ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ አካባቢና ደን ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዮት ብርሃኑ ናቸው። ኢንስቲትዩቱ በአካባቢ የሥነ ምህዳር መራቆት የሚመጣውን የአፈር መከላትና የደን ውድመት ለመከላከል አዳዲስ ቴክኖሎጅዎችን መፍጠር፣ማላመድና ለተጠቃሚው ህብረተሰብ ተደራሽ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። ባለፉት ሁለት ዓመታት 67 የደን ልማት ምርምር ውጤቶችን በማውጣት ለተጠቃሚው ህብረተሰብ ተደራሽ አድርገናል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ለጣውላ ምርት፣ለማገዶ፣ለሃይል ማመንጫና ለሌሎች አገልግሎት የሚውሉ የደን ምርምር ሥራዎች እየተካናወነ መሆኑን ገልፀዋል። በተለይ በቀርከሃና እንቦጭ ለሃይል ማመንጫነት ለማዋልና በጣውላ ዛፎች ልማት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው በዚህም በሙከራ ደረጃ ውጤታማ ሆነን የማስፋት እንቅስቃሴ  እየተከናወነ  መሆኑን አመልክተዋል። በአካባቢ፣በደን ልማትና ጥበቃ፣በዛፍ ዘርና በደን ውጤቶች እንዲሁም በደቂቅ አካላት ልማት ላይ 6 የምርምር ላቦራቶሪዎችና በ25 የዛፍ ዘር ምንጭ ቦታዎች ላይ በርካታ የምርምር ሥራ እየተከናወነ ነው ። የመድረኩ ዓላማ ወደ ሙከራ የገቡና የተጠናቀቁ የምርምር ውጤቶች ለተጠቃሚው ማህበረሰብ ተደራሽ ማድረግ በሚቻልበት ሂደት ላይ ቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥና አዲስ የተቀረፁ የምርምር ፕሮጄክቶችን ለመገምገም ነው ብለዋል። በኢንስቲትዩቱ የደን ተመራማሪ አቶ የአለምሰው አደላው በበኩላቸው እንቦጭን ጨምሮ መጤ አራሞችን ወደ ሃይል ማመንጫነት ለመቀየር የሚያስችል ቴክኖሎጂ በምርምር ማውጣታቸውን ገልጠዋል። ቴክኖሎጂው የእንቦጭ አረም ወደ ተፈጥሮ ማዳበሪያና ሃይል ሰጪነት የሚለውጥ ነው ያሉት ተመራማሪው በዚህም በደን ላይ በማገዶ ምክንያት የሚደርሰውን ጉዳት መቀነስና የውሃ ሀብታችን ይዘቱንና ጥራቱን ጠብቆ በዘላቂነት እንዲቆይ ያስችላል ነው ያሉት። ቴክኖሎጂው በሙከራ ደረጃ ከእንቦጭ አረም እስከ ሁለት ሳዓት የሚነድ ከሰል ለመፈብረክ የሚያስችል ሲሆን አረሙን ለመቆጣጣር ወሳኝ ሚና እንዳለው አስረድተዋል ። በመድረኩ ላይ በደንና አካባቢ የሚሰሩ ተመራማሪዎችና ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን ውየይቱ ለሚቀጥሉት ሦስት ቀናት ይቆያል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም