አለመተማመንና ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ጥረት አለማድረግ በአገሪቱ የሰላም እጦት እንዲባባስ አድርጓል

160
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 9/2012 አለመተማመንና ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ጥረት አለማድረግ በአገሪቱ የሰላም እጦት እንዲባባስና መደማመጥ እንዳይኖር ምክንያት መሆኑን ምሁራን ተናገሩ። አዕላፍ መልቲ ሚዲያ ''ችግሮቻችንን በውይይት መፍታት ለምን ተሳነን'' በሚል ርዕስ ከምሁራንና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ዛሬ በአዲስ አበባ ውይይት አካሂዷል። በውይይቱ የተገኙ ምሁራን እንዳሉት፤ በአገሪቱ በሰላምና በሌሎች ችግሮች ዙሪያ በርካታ ውይይቶች ቢካሄዱም የሚያመጡት ውጤት የሚፈለገውን ያህል አይደለም። ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ እንደሚሉት፤ ውይይት የሰላማዊ ተግባቦት ውጤት ቢሆንም ብዙ ጊዜ የሚደረጉ ውይይቶች አድማጭ ተኮር በመሆናቸው ውጤት አልባ ይሆናል። ''በውይይት መድረኮች ላይ የሚንጸባረቁ የእኔ ብቻ ይሰማልኝ አባዜ፣ ንግግር ለማሳመርና አንዱን ለመጥቀም ተብሎ የሚደረጉ ውይይቶች ሰላማዊ ተግባቦትን ጎድቶታል'' ብለዋል። ዓላማቸውና መዳረሻቸውን ሳይገነዘቡ ውይይት ማዘጋጀትና ያለሙያ ትንታኔን መስጠት አገራዊ መግባባትን ለማምጣት የሚሰራውን ስራ እያደናቀፈ እንደሆነም ጠቁመዋል። በእነዚህና መሰል ለጉዳዮች የምናደርጋቸው ውይይቶች ፍሬ አፍርተው አገርንም ህዝብንም መጠቀም ተስኗቸዋል ባይ ናቸው። ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ ዘካሪያ በበኩላቸው በኢትዮጵያ የተጻፈ ህግ በሌለበት ዘመን ዜጎች ችግሮቻችውን በውይይትና በንግግር የመፍታት ባህላቸው ከፍተኛ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት የሚናገሩ መሆኑን አስታውሰዋል። የተጻፈ ህግ ባለበት ቴክኖሎጂ በረቀቀበት በአሁኑ ዘመን ሰዎች ተነጋግረው ችግሮቻችን በውይይት በቀላሉ መፍታት ተስኗቸው ይስተዋላሉ። ይህም ቀድሞ የነበረንን እሴት በአግባቡ የመጠቀም ልምድ ማነስና የቴክኖሎጂ አጠቃቀማችንን በደንብ ማየት እንዳለብን አመላካች ነገሮች ናቸው ብለዋል። ''የህብረተሰቡ ፍላጎትና ጥያቄ ከስር መምጣት አለበት እንጂ ፖለቲካኛው ወደ ህብረተሰቡ የሚጭነው የውይይት አካሄድ መቅረት አለበት'' ሲሉ ምሁራኑ አስገንዝበዋል። የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሃፊና የአዕላፍ መልቲ ሚዲያ ባለቤት መጋቢ ዘሪሁን  ደጉ እንደተናገሩት በአገሪቱ በፖለቲካኛው ተጽእኖ የታችኛው የህብረተሰብ ክፍል ድምጽና ፍላጎት እየተደመጠ አይደለም። የእስካሁኑ አካሄድ ውጤት ያላመጣው ባለቤቱ ቀጥታ በጉዳዩ ስለማይሳተፍና 'እኔ አውቅልሃለው' በሚሉ ፖለቲከኞችና አመራሮች ስለተሸፈነ እንደሆነም ተናግረዋል። ይህ ደግሞ በአገሪቱ የሚከሰቱ የሰላም እጦቶችና ችግሮችን ለመፍታት የሚደረገው ውይይት ውጤት አልባ እንዲሆን ያደረገው መሆኑን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሃጂ ሙፍት በበኩላቸው በአገሪቱ እየተስተዋለው ያለው አለመግባባት የሰላማዊ ውይይት አለመዳበር ችግር መሆኑን ጠቁመዋል። ''ልጆች ከህጻንነታቸው ጀምሮ መልካም ስብእና ይዘው እንዲያድጉ ቢደረግ በንግግርና በውይይት ችግሮችን መፍታት ቀላል ነበረ'' ብለዋል። ''የሃይማኖት አባቶችም ይሁን መንግስት ይህንን ጉዳይ በትኩረት ባለመስራታችን በንግግርና በውይይት መግባባት ተስኖናል'' በማለት ያለውን ክፍተት አመልክተዋል። የውይይት ተሳታፊዎች እንደሚሉት፤ ችግሮችን መፍታት፣ መደማመጥን፣ መከባበር የኔ ሃሳብ ከሁሉም ይበልጣል፣ የሌለውን አልሰማም የሚለውን አስተሳሰብ ማስቀረትና ለሚደረጉ ውይይቶች ደንብና ህግ ማዘጋጀት እንዲሁም ሚዲያዎችና አመራሮች ፍሬ ያለው ውይይት ማዘጋጀት አለባቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም