ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ግንኙነቷን ታጠናክራለች ---ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ

62
ሀዋሳ ሰኔ 20/2010 ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ግንኙነቷን አጠናክራ ለመቀጠል በትኩረት የምትሰራ መሆኑን የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ አስታወቁ፡፡ በኤርትራው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር የሚመራው የልዑካን ቡድን ዛሬ የሀዋሳ ኢንደስትሪያል ፓርክን ጎብኝቷል፡፡ በጉብኝቱ ወቅት የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ እንዳሉት ኢትዮጵያና ኤርትራ በታሪክና በደም የተሳሰሩ አብሮ የማደግ ተስፋቸው የተጣመረ ሀገራት ናቸው፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የቀረበውን የሰላም ጥሪ  የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፍወርቂ በመቀበል የልዑካን ቡድን መላካቸው ተጋርዶ የነበረውን ጥቁር መጋረጃ የቀደደና የሁለቱ ሀገራት አብሮ የማደግ ተስፋ ማብሰሪያ ጊዜ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የሀገሪቱን ሁኔታ ለማሳየት የኤርትራውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የፕሬዝደንቱ የፖለቲካ አማካሪ ጨምሮ የልዑካን ቡድኑ የሀዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክን እንዲጎበኙ መደረጉን ገልጸዋል፡፡ "ይህ ለኤርትራና ለኢትዮጵያ ህዝቦች የሚያስተላልፈው መልዕክት ትልቅ ነው ።በተጨማሪም ለሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ብቻ ሳይሆን ለአለም አቀፍ ማህበረስብም ጭምር የሚያስተላልፈው መልዕክት እጅግ በጣም ትልቅ ነው "ብለዋል ዶክተር ወቅርነህ፡፡ የልዑካን ቡድኑ መምጣት በሁለቱም ሀገራት ህዝቦች ትልቅ ደስታ የፈጠረ መሆኑን ጠቅሰው የሀዋሳ ከተማ ነዋሪ አቀባበልም ማድረጉን  አመልክተዋል፡፡ ጉብኝቱ በዚህ ብቻ የሚያበቃ እንዳልሆነና ወደፊትም የሁለቱ ሀገራት መሪዎች የሚገናኙበት ሁኔታ እንደሚመቻችና ይህም በቅርብ ጊዜ ይሆናል ብለው እንደሚያስቡ ሚንስትሩ ጠቁመዋል፡፡ " በተጨማሪም ሌሎች ተከታታይ በጋራ በምንሰራቸውና በምንጓዝባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ሁለቱ የውጪ ጉዳይ ሚንስትሮች አጠናክረን እንሰራለን"  ብለዋል፡፡ በጉብኝቱ ወቅት የደቡብ ህዝቦች ክልል ብሄረሰቦች ምክር ቤት ለልዑካን ቡድኑ ስጦታ አበርክቷል፡፡ የኤርትራ መንግሥት የልዑካን ቡድን አባላት ኢትዮጵያ የገቡት ትናንት ሲሆን በአዲስ አበባ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ አቀባበል እንዳደረጉላቸው በወቅቱ ተገልጿል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም