የሚኒስትሮች ምክር ቤት 27 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት እንዲጸድቅ ውሳኔ አሳለፈ

59

አዲስ አበባ የካቲት 9/2012 (ኢዜአ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 79ኛ መደበኛ ስብሰባ የተጨማሪ በጀት ውሳኔ ማሳለፍን ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።

በዚህም ምክር ቤቱ 27 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት እንዲጸድቅ በመወሰን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መርቷል።

የፌዴራል መንግስት የተጨማሪ በጀትና የወጪ አሸፋፈን ማስተካከያ ረቂቅ አዋጅ ላይ የተወያየው የሚኒስትሮች ምክር ቤት፤ለተጨማሪ በጀቱ መሰረታዊ መነሻ የሆነው በቅርቡ በመንግስት የተዘጋጀው የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ እንደሆነ ተገልጿል።

ኢኮኖሚው አሁን ከገጠመው ተግዳሮቶች የሚላቀቅበትን የፖሊሲ እርምጃዎች ለመተግበር 18 ቢሊዮን ብር፤  ለልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ትግበራ ሁለት  ቢሊዮን  ብር እንዲሁም ለእኩል ስራ እኩል ደመወዝ አገራዊ ትግበራ 7 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት እንዲጸድቅ አቅርቧል።

ምክር ቤቱም በቀረበው የተጨማሪ በጀት ረቂቅ አዋጅ ላይ በስፋት ተወያይቶ ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል፡፡

በመቀጠልም ምክር ቤቱ የተወያየው በገንዘብ ሚኒስቴር የቀረቡትን ለደብረ ማርቆስ-ሞጣ የመንገድ ሥራ ማሻሻያ ፕሮጀክት፣ ለአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የልህቀት ማዕከል መመስረቻ ፕሮጀክትና ለሁለተኛው አገር አቀፍ የመጠጥ ውሀ አቅርቦት ሳኒቴሽንና ሐይጅን ፕሮግራም ማስፈጸሚያ የሚውሉ የብድር ስምምነቶችና ማጽደቂያ ረቂቅ አዋጆች ላይ ተነጋግሯል።

ብድሮቹ ከአገሪቱ የብድር አስተዳደር ስትራቴጂ ጋር የሚጣጣሙ፣ የ10 ዓመት እፎይታ ያላቸው፣ በረጅም ጊዜ የሚከፈሉ እንደዚሁም ወለድ የማይታሰብባቸው በመሆናቸው አዋጆቹ ይጸድቁ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ ወስኗል፡፡

ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየበት የአፍሪካ ህብረት ሰንደቅ ዓላማ መዝሙርና የአፍሪካ ቀን ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገሮች ጋር ያላትን አጋርነት ለማሳደግ፣ ለፓን-አፍሪካኒዝምና ለአፍሪካ የውህደት አጀንዳ ተግባራዊነት ያላትን ቁርጠኝነት ለማስቀጠል እንደሚያስችል ተመልክቷል።

እንዲሁም የህብረቱ ኮሚሽን አስተናጋጅ አገርነት ሚናዋን ለመወጣት ከምታከናውናቸው ተግባራት በተጨማሪ አህጉራዊ ሰንደቅ አላማን ማውለብለብ፣ የህብረቱ መዝሙርን ማዘመርና የአፍሪካ ቀን ታስቦ እንዲውል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተላልፏል፡፡

በመጨረሻም ምክር ቤቱ የግብርና ሚኒስቴር አዘጋጅቶ ባቀረበው የግብርና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጆችን ማቋቋሚያ ረቂቅ ደንብ ላይ ተወያይቷል።

ኮሌጆቹ ተጠሪነታቸው ለግብርና ሚኒስቴር ሆኖ ራሳቸውን የቻሉ ህጋዊ ሰውነት ያላቸው ተቋማት እንዲሆኑና በግብርናው ዘርፍ በአገሪቱ ልዩ ፍላጎቶች ላይ እንዲያተኩሩ ለማድረግ ማቋቋሚያ ረቂቅ ደንብ አዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ውሳኔ አቅርቧል፡፡

ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ ከተወያየ በኋላ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማከል ደንቡ በነጋሪት ጋዜጣ እንዲወጣና በስራ ላይ እንዲውል መወሰኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም