ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመከላከል፤ ህዝብን ያሳተፈ ቁጥጥር ይጠይቃል

301
አዲስ አበባ የካቲት 9/2012 ኢዜአ በኢትዮጵያ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመከላከል ህዝብን ያሳተፈ የቁጥጥርና ክትትል ስርአት ሊበጅ እንደሚገባ ተጠቆመ። የሠላም ሚኒስቴር ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ላይ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል። በውይይቱ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት፣ ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽ፣ ከክልል ጸጥታ ቢሮዎች፣ ከመከላከያ ሚኒስቴር፣ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ኤጀንሲን ጨምሮ በርካታ ባለድርሻ አካላት ተሳትዋል። በጠቅላይ ዓቃቤ የሕግ ጥናቶች ማርቀቅና ማከፋፈል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ በላይሁን ይርጋ የአዋጁን አስፈላጊነትና ተፈጻሚነት ወሰን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በአገሪቷ የጦር መሳሪያን በተመለከተ የሕግ ማዕቀፍ አለመኖር በርካታ ችግሮች እንዲከሰቱ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው በተለይ ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን አንስተዋል። አዋጁ የጦር መሳሪያ ከአገር ሲወጣና ሲገባ ማነው ማስተዳደር ያለበት? ፍቃድ አሰጣጡስ እንዴት ይሁን? በሚሉትና በኢትዮጵያ የጦር መሳሪያ ክምችት መጠን አለመታወቁ አዋጁ እንዲወጣ አይነተኛ ምክንያት መሆኑ ተብራርቷል። ''ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር በዜጎች ሠላምና ደህንነት እንዲሁም በአገሪቷ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ስጋት ደቅኗል'' ያሉት ዳይሬክተሩ ለዚህም በምክር ቤቱ አዋጅ መፅደቁን አስታውሰዋል። አዋጁ የመከላከያ ሰራዊትና ብሄራዊ መረጃና ደህንትና አገልግሎትን ሳይጨምር በማንኛውም ሰው ላይ ተፈጻሚ እንደሚሆንም ተመለክቷል። የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የሕግ አገልግሎት ዳይሬክተር ኮማንደር ፋሲል አሻግሬ በተለይ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የዜጎች የደህንነት ስጋት፣ ለኢኮኖሚ ምንጭነት ለማዋልና ለፖለቲካዊ ጉዳዮች ሲባል ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር መጨመር ምክንያት ሆኗል። ''በሕዝብ ማመላለሻ፣ በጭነት መኪና፣ በነዳጅ ቦቴዎች በግመልና የተለያዩ እስንሳት ተጭኖ ይዘዋወራል ያሉት ኮማንደር ፋሲል በኬላዎች ፍተሻ በማድረግ በርካታ ቁጥር ያለው ህገ ወጥ መሳሪያ እየተያዘ ነው ብለዋል። አወጁን ተግባራዊ በማድረግ በቀጣይ ውጤታማ ቁጥጥር ለማድርግ ሕዝቡ በቅንጅት እንዲሰራ ግንዛቤውን ማስፋት ተገቢ ይሆናልም ነው ያሉት። በጸጥታ አካላት በርካታ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር እየዋሉ ቢሆንም በቀጣይ የቁጥጥር ስራውን ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል። የደቡብ ክልል ሠላምና ጸጥታ ቢሮ ተወካይ አቶ ኃይሉ ማቲዎስ እንደሚሉትም ''ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን በዘላቂነት ለመግታት ሰንሰለቱን መበጠስ'' ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ሕዝቡን በስፋት የሚያሳትፍ ስርዓት ሊዘረጋ ይገባል ብለዋል። ከወንጀሉ ውስብስበት አንጻር ሕግ በማውጣት ብቻ ችግሩን መፍታት ስለማይቻል ከህዝቡ ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል። በግለሰቦች እጅ ያለው በርካታ ጦር ማሳሪያ ህጋዊ የሚሆንበትን መንገድ የመቻቸት ጉዳይ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባም ጠቁመዋል። ''አዋጁ በጣም ዘገይቷል እስካሁን ብዙ ጉዳቶች ደርሰዋል በአፋጣኝ ወደ ሥራ ሊገባ ይገባል'' ያሉት ደግሞ ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ የደቡብ ክልል ሚሊሻ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መርዕድ ዲዳ ናቸው። ፈቃድ ያልተሰጠው የጦር መሳሪያ ታጥቀው የሚገኙ በርካታ አርሶና አብርቶ አደሮችም ህጋዊ ሆነው እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ ይገባል ብለዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም