በአፍሪካ ቀንድ የሃያላን አገራት ወታደራዊ ቤዝ ማጠናከርና የኢትዮጵያ አካሄድ ወዴት ያመራል?

382
አዲስ አበባ የካቲት 8ሐ2012 (ኢዜአ) በአፍሪካ ቀንድ የሃያላን ሀገራት ወታደራዊ ቤዝ ማጠናከርና የኢትዮጵያ መፃኢ እድልና የምሁራን እይታ:: በምስራቅ አፍሪካና አካባቢው ካለው የጂኦ ፖለቲካ ስትራቴጂ አኳያ በርካታ ሃያላን አገራት ወታደራዊ ይዞታቸውን ማስፋትና ማጠናከር ከያዙ ውለው አድረዋል። የአፍሪካ ቀንድ የሶስት አሀጉራት ማለትም የአፍሪካ፣ እሲያና አውሮፓ መገናኛ እንብርት መሆኑ ለሃያላኑ አገራት ወታደራዊ ይዞታ እሽቅድምድም አይነተኛ ምክንያት መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ይናገራል። ቀጠናው የአለማችን የነዳጅና ሌሎች እቃዎች አቋራጭ ማጓጓዣ መሆኑም ሌላው ምክንያት ነው። በዓለም ኢኮኖሚና የንግድ እንቅስቃሴ እንዲሁም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ላይ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ወሳኝ መሆኑም ብዙዎችን ያስማማል። ለዚህም ነው አሜሪካን ጨምሮ ቻይና፣ ፈረንሳይ፣ ሩሲያ፣ ቱርክ፣ ሳኡዲ አረቢያና ሌሎችም አገሮች ወታደራዊ ይዞታቸውን በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያደረጉት። በቀይ ባህርና በምስራቅ አፍሪካ ቀንድ ላይ ጥናት ያደርጉ የፖለቲካ ተንታኞች ምስራቅ አፍሪካን "ገሃነማዊ ገነት" ሲሉም ይጠሩታል። የምስራቅ አፍሪካ በየነ መንግስታት የሰላምና ፀጥታ ዘርፍ ዳይሬክተር ኮማንደር አበበ ሙሉነህ " ምስራቅ አፍሪካ እና የሃያላኑ የጦር ይዞታ" እንዴት ይታያል የሚለውን ከኢዜአ በነበራቸው ቆይታ ማብራሪያ ሰጥተዋል። እርሳቸው እንደሚሉት በቀጠናው የሃያላን አገራት የጦር ቤዝ ምስረታና መስፋፋት እንዲሁም ሽኩቻ የቀጠናውን ሰላም የተወጠረ እንዲሆን አድርጎታል። እንደ ኮማንደር አበበ ገለፃ በቀጠናው የሃያላኑ አገራት ወታደራዊ ፉክክር፣ መደጋገፍና ተቃርኖ በአካባቢው አገሮች ዘንድ ጭምር አንዴ ሞቅ ሌላ ጊዜ ቀዝቀዝ የሚል ፖለቲካዊ ወላፈን እየፈጠረ ነው። በዚህም አጋጣሚ በአካባቢው የተለያዩ ህገ ወጥ ቡድኖችና ሽብርተኞች እንዲንቀሳቀሱ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ይላሉ። በቀጠናው ሀገራት የሚታየው የድንበር ተሻጋሪ ወንጀል፣ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ የጦር መሳሪያ ንግድና ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርም የአካባቢውን የፖለቲካ ውጥረት እንደ ምቹ ሁኔታ ይጠቀሙበታል። የቀጠናው ሀገራት በእነዚህ ችግሮች ላይ በቁርጠኝነት በሚሰሩት ልክ ችግሩ መቀነስ ያልቻለበት ምክንያትም በገሃድ የማይታዩ ስውር እጆች በመኖራቸው ነው ይላሉ። በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ የዲፕሎማሲና ዓለም አቀፍ ትምህርት ክፍል ሃላፊና መምህር እንዳለ ንጉሴ በበኩላቸው ኢትዮጵያ እየተከተለችው ያለው የውጭ ፖሊሲ የሁሉም አገሮች ትኩረት እየሆነች መጥታለች። የተለያየ ፖለቲካዊ አቋም ይዘው ከኢትዮጵያ ጋር ጥብቅ የሆነ የኢኮኖሚ፣ ፖለቲካና የዲፕሎሲ አጋርነታቸውን የቀጠሉ አገራት እየተበራከቱ መሆኑንም ገልጸዋል። ለዚህም ዋና ምክንያቱ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ከጥንት ጀምሮ በአንፃራዊነት የፖለቲካ ገለልተኝነትን የሚከተልና ከሁሉም ጋር ወዳጅነትን ማጠናከር መርህ በማድረጉ ነው ብለዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገር ውስጥና በውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋ ላይ እያመጣች ያለው አካሄድ በሁለት ጎራ የተከፈለውን የአለም ፖለቲካ ከብሄራዊ ጥቅሟ ጋር አጣጥማ እንዲትቀጥል አስችሏታልም ይላሉ። በውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋን በመደመር እሳቤ በመቃኘት የጀመረችው አካሄድም አካባቢውን ከውጥረት ይልቅ ወደ መረጋጋት እንዲያመራ እያደረገው መሆኑን አንስተዋል። ኢትዮጵያ መተግበር የጀመረችው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲም ብሄራዊ ጥቅሟን መሰረት ያደረገና የዜጎችን ክብርና ደህንነት ማእከል ያደረገ  መሆኑን ተናግረዋል። በቀይ ባህር አካባቢ ያለው አለም አቀፍ ፖለቲካዊ ፉክክርና እሽቅድምድም ኢትዮጵያ እየተከተለችው ካለው የውጭ ፖሊሲ አኳያ ሲታይ ተፅእኖ እንደሌለው ያስረዳሉ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም