ከበልግ ልማት የተሻለ ምርት እንጠብቃለን - የወላይታ ዞን አርሶ አደሮች

113
ሀዋሳ ሰኔ 20/10/2010 በድርቅና ተምች ምክንያት ባለፈው ዓመት ያጡትን በዘንድሮው የበልግ ወቅት ማካካስ የሚያስችል የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የወላይታ ዞን አርሶ አደሮች ገለፁ፡፡ በዞኑ ከጥር አጋማሽ እስከ ሰኔ መጨረሻ በሚካሄደው የበልግ ልማት 148 ሺ ሄክታር መሬት በተለያየ ሰብል መልማቱን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት መምሪያ አስታውቋል፡፡ አርሶ አደር ፍራንሶ መስቀሌ አረካ ወረዳ የአደዳሞት ቀበሌ ነዋሪና የአምስት ልጆች አባት ሲሆኑ መተዳደራቸውም ግብርና ነው፡፡ ባለፈው ዓመት በአካባቢያቸው ተከስቶ የነበረው ድርቅና ተምች የቤተሰባቸውን ኑሮ ፈትኖ እንዳለፈ ተናግረዋል፡፡ “ልጆቼን እቀልብበታለሁ፣ ኑሮየን አሻሽልበታለሁ ብዬ  በዘር የሸፈንኩት ማሳ በተከሰተው ችግር ምክንያት ምርት አልባ በመሆኑ ለቀለብ መግዣ የእርሻ በሬ ጭምር ሽጫለሁ'' ብለዋል፡፡ አንድ ሄክታር በሚጠጋ ማሳቸው በቆሎ፣ አደንጓሬና ጎዶሬ የሚያመርቱት አርሶአደሩ ዘንድሮም ተመሳሳይ ችግር ይገጥመኛል የሚል ስጋት የነበራቸው ቢሆንም የዝናቡ ስርጭትና መጠን ለልማቱ ተስማሚ በመሆኑ ከዘንድሮው የበልግ ልማት የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡ እንዲሁም ባለፈው የምርት ዘመን ገጥሟቸው የነበረው የተምች ወረርሽኝ እስካሁን በማሳቸው አለመከሰቱም ባለፈው ዓመት ያጡትን ለማካካስ የሚያስችል የተሻለ ምርት ማግኘት እንደሚያስችላቸው አስታውቀዋል፡፡ ሌላኛው አርሶ አደር ዳንኤል ሱፑራ ባለቸው ማሳ ድንች፣ አደንጓሬና በቆሎ የሚያመርቱ ሲሆን  በማሳቸው ተምቹ በታየ ጊዜ በእጅ እየገደሉ ማጥፋታቸውን ተናግረዋል፡፡ ደጋግመው እንዲያርሱ፣ ምርጥ ዘርና የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በሚገባ እንዲጠቀሙ በማድረግ የዞኑ ግብርና ባለሙያዎች እገዛ አልተለያቸውም፡፡ የዘሩት 540 ቢ ኤች የተሰኘ የበቆሎ ምርጥ ዘር ጥሩ እንደያዘላቸውና ከራሳቸው የቀን ቀለብ አልፎ ለገበያ ሊያቀርቡ የሚያስችል አያያዝ ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡ ፍራፍሬ፣ ጅንጅብል፣ ቡና፣ በቆሎና ሌሎችንም አዝእርቶች የሚያለሙት የቦሎሰ ሶሬ ወረዳ አርሶ አደር ዘውዴ ለንበቦ በበኩላቸው ባለፈው ዓመት ከድርቅና ተምች ወረርሽኝ የተነሳ ያጡትን ምርት የሚያካክስ የሰብል ምርት ሊያገኙ እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡ የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት መምሪያ ኃለፊ አቶ ክፍሌ ታውለ እንዳሉት በዞኑ ከጥር አጋማሽ እስከ ሰኔ መጨረሻ ባለው የበልግ ወቅት 148 ሺ ሄክታር መሬት በልዩ ልዩ የሰብል ዘር መሸፈኑን ገልፀዋል፡፡ ለዚህም የሚሆን ከ170 ሺህ በላይ የአፈር ማዳበሪያና ከ10 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ጥቅም ላይ መዋሉን ጠቁመዋል፡፡ በዘር ከተሸፈነው መሬት ውስጥ በ321 ሄክታር ላይ ተከስቶ የነበረው ተምች ከአርሶ አደሩ ጋር በተደረገ ጥረት መቆጣጠር መቻሉን ተናግረዋል፡፡ የተምች ስጋቱ ሙሉ በሙሉ መወገዱ፣ በቂ የዝናብ መጠን መኖሩ፣ አስተማማኝ የግብዓትና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም የተስተዋለበት ወቅት በመሆኑ ከበልግ ልማት ለመሰብሰብ የታቀደውን 23 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚሳካ ተናግረዋል፡፡ ባለፈው የምርት ዘመን በተመሳሳይ የእርሻ ወቅት 21 ሚሊዮን ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ 18 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መገኘቱንም አስታውሰዋል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም