የገዳሪፍ ልዑካን ቡድን በባህርዳር ከተማ የልማት ስራዎችን ጎበኘ

86
ባህርዳር፣ የካቲት 8/2012 (ኢዜአ) የሱዳን የገዳሪፍ ግዛት የልዑካን ቡድን አባላት በባህርዳር ከተማ የሚገኙ የተለያዩ የልማት ስራዎችንና የጣና ገዳማትን ተዘዋውረው ጎበኙ። ጉብኝቱን አስመልክተው የክልሉ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አቻምየለህ ካሳ እንደገለጹት የልዑካን ቡድኑ በባህርዳር የልማት ስራዎችን ዛሬ ተዘዋውሮ መጎብኘቱ ጠቀሜታው የጎላ ነው። ልዑኩ ከጎበኛቸው የልማት ስራዎችና የተፈጥሮ ሃብቶች መካከልም የጣና ገዳማትን ጨምሮ የአማራ ቧንቧ ፋብሪካ፣ የኤጅ የቧንቧ መገጣጠሚያ ፋብሪካና የባህርዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ ይገኙበታል። በተለይ በርዝመቱ የሚታወቀውና ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅን በጋራ የሚያስተሳስረውን የአባይ ወንዝ ከጣና ኃይቅ ለቆ የሚወጣበትን ቦታ መጎብኘታቸው የልዑካን ቡድኑን ትኩረት የሳበ እንደነበር ገልጸዋል። ሌላው የልዑካን ቡድኑ ትኩረት የሳበው የኤጂ የቧንቧ መገጣጠሚያ ፋብሪካ ከሚያመርታቸው አንዱ የፕላስቲክ ውጤቶች ሲሆን በተለይ ለስታዲየም የሚገጠሙ የፕላስቲክ ወንበሮችን በቀጣይ ለመጠቀም ፍላጎት አሳይተዋል። በሱዳን የገዳሪፍ ግዛትና በኢትዮጵያ የአማራ ክልል የሁለቱን ሀገራት ሰፊውን የድንበር ወሰን የሚጋሩ በመሆናቸው ጉብኝቱ በጋራ ተጋግዘው ለማልማትና ለማደግ ፋይዳው የጎላ ነው። ሀገራቱ የአባይን ውሃ በጋራ የሚጠጡና የሚያለሙ ከመሆናቸውም በላይ የሁለቱ መንግስታትና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ይበልጥ እንዲጠናከር የሚኖረው ጠቀሜታም ከፍተኛ እንደሆነም ዳይሬክተሩ አስረድተዋል። ከ20 በላይ አባላት ያሉት የገዳሪፍ ግዛት የልዑካን ቡድን አባላት ትናንት ባህርዳር ሲገባ በከተማው ከንቲባና በነዋሪዎች ደማቅ አቀባበል መደረጉ ይታወሳል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም