የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ 221 የህክምና ዶክተሮችና ስፔሻሊስቶችን አስመረቀ

88
ሀዋሳ፣ የካቲት 8/2012 (ኢዜአ) የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ምንጮች ብቻ ሳይሆኑ በመልካም ሥነ-ምግባር የታነፀ ዜጋን ማፍሪያ ማዕከላት ጭምር መሆን እንዳለባቸው የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አሳሰቡ። ዩኒቨርሲቲው 192 የህክምና ዶክተሮችና 29 ስፔሻሊስት ዶክተሮች ዛሬ አስመርቋል። በምረቃ በዓሉ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አያኖ በራሶ እንደገለፁት ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ወቅት በመጀመሪያ ዲግሪ፣ በሁለተኛ ዲግሪ፣ በህክምና ስፔሻሊስትና በሶስተኛ ዲግሪ በርካታ ፕሮግራሞችን በመክፈት ከ43 ሺህ 800 በላይ ተማሪዎችን በመደበኛና በተከታታይ ትምህርት መርሀ ግብሮች እያስተማረ ይገኛል። ከዛሬዎቹ 221 ተመራቂዎች ውስጥ 22 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውንም ጠቁመዋል። የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅም የመምህራን ልማት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡ ሀገሪቱ ካላት ውስን ሀብት ላይ አንድ አራተኛውን በጀት ለትምህርት ማዋሏን የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ ተመራቂዎችም ያላቸውን ዕውቀት፣ ክህሎትና ጉልበት ላስተማራቸው ማህበረሰብ በማበርከት ለሀገራቸው ዕድገት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ምንጮች ብቻ ሳይሆኑ በመልካም ሥነ-ምግባር የታነፀ ዜጋን ማፍሪያ ማዕከላትም ናቸው ያሉት ፕሬዚዳንቱ ተመራቂዎች ራሳቸውን ከመጥፎ ምግባር በመቆጠብና ሙያው በሚጠይቀው ሥነ-ምግባር ህሙማንን በፍቅር ማገልገል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡ በምረቃ በዓሉ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ አባል ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በበኩላቸው ለተመራቂዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ፕሮፌሰር በየነ እንዳሉት ሀገሪቱ ባለፉት ሃያና ሰላሳ ዓመታት ውስጥ በጤናው ዘርፍ በተከናወኑ ተግባራት የተሻለ እመርታ በማስመዝገብ የዓለም ጤና ድርጅትን ጨምሮ ሌሎች ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ታላላቅ ዓለም ዓቀፍ ተቋማትና መንግስታት ዕውቅና ማግኘቷን ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም የጤና ሽፋንን ከመጨመርና ጥራትና ፍትሐዊነት ያለው አገልግሎት ከመስጠት አንጻር ብዙ ርቀት መጓዝ እንደሚጠይቅ የተናገሩት ፕሮፌሰር በየነ የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት ጠንክረን በጋራና በትብብር መንፈስ መስራት አለብን ብለዋል፡፡ የዛሬ ተመራቂዎችም የነገዋ ኢትዮጵያ ተስፋዎች መሆናቸውን በመረዳት ሀገራቸውን ማገልገል እናዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡ በሙያቸው ገፍተው ዕውቀትና ክህሎታቸውን በማዳበርም የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡና ችግር ፈቺ በሆኑ ምርምሮች ውስጥ በመሳተፍ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተተገበረ ያለውን ፈርጀ ብዙ ለውጥ የማቀጣጠልና የማስቀጠል ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል ፡፡ ከተመራቂዎች መካከል ከፍተኛ ውጤት በማምጣት የሜዳልያ ተሸላሚ የሆነው ዶክተር አቤል ጌታቸው በሰጠው አስተያየት የህክምና ትምህርት ጽናትን የሚጠይቅ መሆኑን ገልፆ ሁኔታዎችን በትዕግስት በማለፍ ለዚህ መብቃቱን ተናግሯል፡፡ የህክምና ሙያ በራሱ ለሰዎች ክብር መስጠትና ርህራሄ መላበስን የሚያስተምር እንደሆነ የተናገረው ዶክተር አቤል ያለአድሎ ሰብአዊነትን በመላበስ ህብረተሰቡን ለማገልገል ዝግጁ መሆኑን አስረድቷል ፡፡ በውስጥ ደዌ ህክምና ስፔሻላይዝድ በማድረግ የተመረቀው ዶክተር ሙባረክ ሁሴን በበኩሉ የህክምና ሥነ-ምግባር ከሀሳብ ይልቅ በተግባር የሚገለፅ መሆኑንና ታካሚዎችን እንደ ቤተሰብ በማየት ያለአድልኦ ለማገልገል መዘጋጀቱን ተናግሯል፡፡ ኮሌጁ የህክምና ዶክትሬት ተማሪዎችን ሲያስመርቅ ለ11ኛ ዙር ሲሆን ስፔሻሊስት ሀኪሞችን ደግሞ ለ4ኛ ዙር ነው ተብሏል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም