በወላይታ ምርታማነትን የሚያሳድጉ 25 የቡና ዝርያዎች የማላመድ ስራ እየተከናወነ ነው

76
ሶዶ፣ የካቲት 8/2012 (ኢዜአ) በወላይታ ዞን በአሳሳቢ ደረጃ እየቀነሰ የመጣውን የቡና ምርት እንዲያንሰራራ ለማድረግ 25 አዳዲስ የቡና ዝርያዎችን ከአካባቢው ጋር የማላመድ ስራ እያከናወነ መሆኑን የወላይታ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ። ዩኒቨርሲቲው ከጅማና ከአዋዳ ግብርና ምርምር ማእከላት የተቀበላቸው 25 የተሻሻሉ ምርጥ የቡና ዝርያዎች በዞኑ በሚገኙ ሶሰት ወረዳዎች የአየር ፀባይና ከተለያዩ የአፈር ዓይነቶች ጋር የማላመድ ስራ እያከናወነ መሆኑን አስታውቋል። የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ ምክትልና የቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ተስፋዬ ጉአ እንደሚሉት ከሆነ በዞኑ ቡና አምራች በሆኑ አካባቢዎች ቀደም ሲል በሄክታር 8 ነጥብ 5 ኩንታል ምርት ይገኝ ነበር። አርሶ አደሩ ለቡናው የሚያደርገው እንክብካቤ መቀነስና ያረጀ ቡናን በጉንደላ ባለማደሱ ምርቱ እየቀነሰ መምጣቱን ጠቁመው በአሁኑ ወቅት ከሄክታር የሚገኘው ምርት በ3 ነጥብ 2 ኩንታል ዝቅ ማለቱን ገልጸዋል። በተያዘው ዓመት ከዞኑ ለማዕከላዊ ገበያ 3 ሺህ 117 ቶን ቡና ለማቅረብ ቢታቀድም ማቅረብ የተቻለው 2 ሺህ 80 ኩንታል ብቻ መሆኑን ተናግረዋል። ለምርት መጠኑ መቀነስ ያረጀና ምርታማነቱ የቀነሰ ቡናን ካለማደስ በተጨማሪ በዘር መረጣ፣ በችግኝ ዝግጅት፣ በተከላና እንክብካቤ ዙሪያ ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶች ይጠቀሳሉ። በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ኮሌጅ ዲን አቶ አስራት ወርቁ እንዳሉት ኮሌጁ በዞኑ ከቡና ልማት ጋር ተያይዞ የሚስተዋለውን ችግር በመለየት የተሻለ መፍትሔ ለማምጣት እየሰራ ይገኛል። “በዞኑ የቡና ምርት መጠን በተያዘው ዓመት በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል” ያሉት በኮሌጁ የሆርቲካልቸር ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ዶክተር አብርሀም ሹምቡሎ በበኩላቸው እግሩን መሰረት ያደረገ ምርምር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።አርሶ አደሩ ከአካባቢው ስነ-ምህዳር ጋር ተስማሚ የሆነ ዝርያ ያለመምረጥ፣ ተገቢውን እንክብካቤ ያለማድረግ፣ ያረጀውን ቡና ያለመጎንደልና ከምርት አሰባሰብ ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ጉድለቶች በጥናት ተለይተዋል። ችግሩን ለመፍታት በዞኑ ሶስት ወረዳዎች ሰርቶ ማሳያዎችን በማዘጋጀት ከጅማና አዋዳ ግብርና ምርምር ማዕከላት 25 ዝርያዎችን በማስመጣት የማላመድ ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል። በቡና ልማት ላይ የተሰማሩት የኦፋ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር መስቀሌ ጌታ በበኩላቸው ከቡና ዘር መረጣ እስከ ተከላና እንክብካቤ የሚያከናውኑት ስራ ልማዳዊውን መንገድ በመከተል ነው። በማሳቸው ያለው ቡና ረጅም ጊዜ ከመቆየቱ ባለፈ ተገቢውን እንክብካቤ ባለማድረጋቸው ምርቱ መቀነሱን ገልጸዋል። አሁን ግን ኮሌጁ በሚያደርግላቸው ድጋፍ በመታገዝ ያረጀ ቡናቸውን በመጎንደል የማደስና የተሻሻሉ አዳዲስ የቡና ዝርያዎችን በመትከል ምርታማነታቸውን ለማሳደግ እንደሚሰሩ ገልፀዋል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም