የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ኢትዮጵያውንን ያስከበሩ ተግባራት የተከናወኑበት ነው - አቶ ንጉሱ ጥላሁን

123
አዲስ አበባ፣ የካቲት 8/2012 (ኢዜአ) የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ጉብኝት ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ያስከበሩ ተግባራት የተከናወኑበት መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬተሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ተናገሩ። በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በመጠለያ ይኖሩ የነበሩ 135 ኢትዮጵያውያንም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ ጋር ወደ አገራቸው ተመልሰዋል። በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የኢትዮጵያ አምባሳደር ሱለይማን ደደፎ እንደገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የተለያዩ የመንግስት ኃላፊዎች ጋር ያደረጉት ውይይት ውጤታማ ሆኗል። በዚህም በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በህገ ወጥ መንገድና በመጠለያ ጣቢያዎች ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ መደረጉን አቶ ንጉሱ ገልጸዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት የዜጎች አጠቃላይ ሁኔታን ተረድቶ መብቶቻቸውና ጥቅሞቻቸው እንዲከበርና በዘላቂነት በዜግነታቸው ክብራቸው ተረጋግጦ እንዲኖሩ ለማድረግ ነው። ለዚህም ይረዳ ዘንድ ከጉብኝታቸው አስቀድሞ 300 ከሚሆኑ የኮሚኒቲ አመራሮች፣ ከአምባሳደሮች፣ ከቆንስላ ጽህፈት ቤቶችና ሌሎችም ጋር በችግሮቹ ላይ አስቀድመው ውይይት አካሂደዋል። በውይይቱም በችግር ውስጥ ስለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ስለሌላቸው ዜጎች ስለ አምልኮ ቦታ ጥያቄዎችና ሌሎችም ጥያቄዎች ተነስተዋል። እንደ አቶ ንጉሱ ገለጻ የአምልኮ ቦታ ችግሮችን በመፍታት ዜጎች በነጻነት በማምለኪያ ስፍራ የሚሰባሰቡበትን ቦታ የማመቻቸት ስራ ተሰርቷል። ኢትዮጵያውያን ልጆቻቸው ባህላቸውንና ወጋቸውን ታሳቢ ያደረገ የመማሪያ ስፍራ እንዲያገኙ የማስፈቀድ ሥራ መሰራቱን አቶ ንጉሱ ገልጸዋል። "ከከፍተኛ አመራሮች ጋር በመወያየት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ቀደም ሲል ይነሱ የነበሩ ጥያቄዎች ምላሽ ተሰጥቶባቸዋልም" ነው ያሉት። ጉብኝቱም የኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊያን መብትና ክብር ያስጠበቀ መሆኑንም አቶ ንጉሱ ጠቅሰዋል። ከመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት የተውጣጡ ከ15 ሺህ የሚልቁ ኢትዮጵያውያን በዱባይ አል አህሊ ስታዲየም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ተወያይተዋል። በቀጣይም ህገ-ወጥ ደላሎች በዜጎች ላይ የሚያደርሱትን ችግር በጋራ ለመፍታት ከአገራቱ ጋር ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ጠቁመዋል። ኢትዮጵያውያን ህገ-ወጥ ደላሎች በዜጎች ላይ የሚያደርሱትን በደልና ችግር ከምንጩ ለማድረቅ መንግስት በቁርጠኝነት ለመስራት አቋም መያዙንም አቶ ንጉሱ አረጋግጠዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም