በመስቀል አደባባይ የተፈጸመው የጥፋት ተግባር ህዝቡ ለአንድነቱ ይበልጥ እንዲነሳሳ ያደርጋል...የገንዳውሃ ከተማ ነዋሪዎች

50
መተማ ሰኔ 20/10/2010 "ለውጥ እንደግፍ ዴሞክራሲን እናበርታ" በሚል መርህ በመስቀል አደባባይ ለድጋፍ በወጡ ሰላማዊ ዜጎች ላይ የተፈጸመው የጥፋት ተግባር ህዝቡ ለአንድነቱ ይበልጥ እንዲነሳሳ ያደርጋል ሲሉ በምዕራብ ጎንደር ዞን የገንዳውሃ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡት የከተማው ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ አሰለፍ የሽዋስ እንዳሉት ፍቅርንና መቻቻልን ለሚጠላ አስተሳሰብ ዋነኛ ማሸነፊያ መንገድ አንድነትን ማጠናከር ነው። ጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር አብይ በአጭር ጊዜ ቆይታቸው በኢትዮጵያውያን መካከል ለበርካታ ዓመታት ተፈጥሮ የነበረውን የእርስ በእርስ መጠራጠርና መከፋፈል አደጋ እንዲቀለበስ መንገድ የጠረጉ መሪ መሆናቸውን ገልጸዋል። በተለይ አብሮነትን፣ አንድነትን፣ መቻቻልንና ለለውጥ መደመርን በማቀንቀን መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ ለለውጥ በአንድነት እንዲተሳሰር ያደረጉና ለህዝብ ተስፋ መሆን የቻሉ መሪ መሆናቸውን አመልክተዋል። ይህን መልካም ጅምር ስራቸውን ለማበረታታትና ዴሞክራሲን ለማበረታታት አደባባይ በወጣ ህዝብ ላይ ቦምብ ማፈንዳት ህዝቡ የበለጠ ጠንካራ አንድነት እንዲፍጠር የሚያደርግ እንጂ ተስፋ የሚያስቆርጥ አለመሆኑን አስረድተዋል። " በሰልፉ ላይ በተፈጸመው እኩይ ተግባር የሴት ተጠርጣሪዎች መኖሩ በራሱ አስተማሪ መሆኑን ጠቅሰው፣ ወንጀለኞችን ለፀጥታ አካላት አሳልፎ ለመስጠት ህዝቡ ያደረገው ተሳትፎ ይበል የሚያሰኝ መሆኑን አመልክቷል። "ጠቅላይ ሚንስትሩ በወቅቱ ' በአንድ ጠማማ ዛፍ ምክንያት ደኖች አይለቁ' ማለታቸው ፀረ-አንድነትና ፀረ-ህዝብ አመለካከት ያላቸው ግለሰቦች መኖራቸውንና በቀጣይ የማጥራት ሀሳብ እንዳላቸው የሚጠቁም ነው" ያሉት ደግሞ አቶ አስሬ ባየው የተባሉ የከተማዋ ነዋሪ ናቸው። "ኢትዮጵያ የህዝቡን የልብ ትርታ ያዳመጠና ለችግሮቿ መፍትሄ የሚሰጥ መሪ በማግኘቷ ደስተኛ ነኝ" ብለዋል። ወጣት በላይ ድረስ በበኩሉ " የመስቀል አደባባዩ ክስተት ወጣትነት አስተዋይነትና ሚዛናዊነትን ከታከለበት ማንኛውንም እኩይ ተግባር ማሸነፍና ማክሸፍ እንደሚያስቻል ያየሁበት ነው፡፡" ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመጡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ህዝቡ ለረጅም ጊዜ ሲያነሳቸው የነበሩ ችግሮችን በመፍታት በኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል የቀደመ አንድነትና ኢትዮጵያዊነት እንዲታደስ ማድረጋቸውን አመልክተዋል። በቅርቡ የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ በማይደግፉ አካላት በአዲስ አበባ የተካሄደው የቦንብ ጥቃት የወጣቱን ተስፋ ማጨለም የሚፈልጉና ጥላቻ የሚዘሩ አካላት ድርጊት በመሆኑ እንደሚያወግዘው ገልጿል። አጥፊዎች ለህግ እንዲቀርቡ የጠየቀው ወጣቱ፣ ለድጋፍ በወጡ ዜጎች ላይ የተፈጸመው እኩይ ተግባር ህዝቡ አንድነቱን ይበልጥ እንዲያጠናክር ከማድረግ ውጪ የሚኖረው ፋይዳ እንደሌለ ተናግሯል። ባለፈው ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም በተካሄደው ታሪካዊ ሰልፍ ለተሰው ሰማዕታት ቤተሰቦችና ለመላው አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን መጽናናት እንደሚመኙ አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጸዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም