የጤና ቢሮው የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በቅንጅት እየሰራ ነው

81

መቀሌ ኢዜአ የካቲት 07/2012፡- የትግራይ ክልል ጤና  ቢሮ የኮሮና ቫይረስ በሽታ የቅድመ መከላከል ስራዎችን  ከፌዴራል ጤና ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገለጸ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ ዶክተር ሪአ ኢሳያስ ዛሬ ለኢዜአ እንዳሉት ቫይረሱን ለመከላከል ከሚኒስቴሩ ጋር  የጋራ እቅድ በማውጣት እየሰሩ ናቸው።

በመቀሌ አሉላ አባነጋ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን  ማረፊያ ጊዜያዊ የምርመራና ለይቶ የመከታተያ ማዕከል መቋቋሙንም አስታውቀዋል።

ቢሮው የጤና ባለሙያዎችን በመመደብ ወደ አካባቢው  የሚመጡ ሰዎች አስፈላጊውን ክትትልና የጤና ምርመራ እያደረገ መሆኑን ዶክተር ሪአ ገልጸዋል።

ብዛት ያላቸው ሰራተኞች በሚንቀሳቀሱባቸው የኢንዳስትሪ ፓርኮች፤ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና የስደተኞች መጠሊያ ጣቢያዎች ላይም በተመሳሳይ እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

እስካሁን የኮሮና ቫይረስ ምልክት የታየበት ሰው ባይገኝም ኢትዮጵያ በምትዋሰንባቸው የሱዳን አካባቢዎች ጭምር ለመከላከል በትኩረት ክትትል እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

የኮሮና ቫይረስ ከሚተላለፍባቸው መንገዶች  በእስትንፋስ፣ በማስነጠስ፣ በሌሎች የንፅህና ጉድለቶችና በመሆኑ ለማህበረሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በመቀሌ  ሆስፒታል የውስጥ ደዌ በሽታዎች ከፍተኛ ባለሙያ ዶክተር ብስራት ተስፋዬ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም