የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል ቤተ-ክርስትያን በድጋፉ ሰልፍ ለተጎዱ ዜጎች 200 ሺህ ብር ሰጠች

50
አዲስ አበባ ሰኔ 20/2010 የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል ቤተ-ክርስትያን በድጋፉ ሰልፍ ለተጎዱ ዜጎች የ200 ሺህ ብር ድጋፍ አደረገች። የድጋፍ ብሩን በመስቀል አደባባይ በድጋፉ ሰልፍ ለተጎዱ ዜጎች የገንዘብ እርዳታ አስተባባሪ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው ተቀብለውታል። ድርጊቱ ከኢትዮጵያዊ ብቻ ሳይሆን ከማንኛውም የሰው ልጅ የማይጠበቅና  ሊወገዝ የሚገባው ነው ሲሉ የገለጹት የቤተ ክርስትያኒቷ ፕሬዚዳንት ፓስተር ይልማ ዋቄ ናቸው። በቤተክርስትያንዋ ስም ከዚህ በፊት የደም ልገሳ ሰብዓዊ እርዳታ መደረጉን አስታውሰው ከአሁን በኋላም የሚደረግ ሰብዓዊ እርዳታ አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል ፕሬዚዳንቱ። ህይወታቸው ላለፉ ዜጎች መንግስተ ሰማያትን፤ ለቤተሰቦቻቸው መፅናናትን፤ ለቆሰሉ ማገገምን ተመኝተዋል። አቶ አባተ ስጦታው ቤተ-ክርስትያንዋ ላደረገችው ሰብዓዊ ድጋፍ በተጎዱ ቤተሰቦች ስም አመስግነዋል። በቀጣይም ከተማ አስተዳደሩ የእርዳታ ድጋፉን የማስተባበር ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልና በግለሰቦች የሚደረጉ ድጋፎች እንዳይባክኑም በከተማ አስተዳደሩ በኩል እንዲሆን ለህብረተሰቡ ጥሪ አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም