“ማዶ ለማዶ” – ግብጽና የውሃ አጠቃቀሟ

182

ማዶ ለማዶ” – ግብጽና የውሃ አጠቃቀሟ (በሰለሞን ተሰራ-ኢዜአ)

”የናይል ውሃ ላይ የላይኛው ተፋሰስ አገሮች ምንም መጠቀም የለባቸውም” የሚል አይነት አቋም በመያዝ የምትታወቀው ግብጽ የውሃ አጠቃቀሟን ማስተካከል ካልቻለች በናይል ዙሪያ የሚደረጉ ድርድሮች በቀላሉ መፍትሄ ማግኘት እንደማይችሉ በርካታ የዘርፉ ምሁራንና ተንታኞች በተደጋጋሚ ይገልጻሉ።

ለአብነትም ኢትዮጵያ እየገነባችው ባለው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታና የውሃ አሞላል ሂደትን እንኳን ብንመለከት እንኳን በከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች አማካኝነት እየተደረገ ያለው የድርድር ሂደት መቋጫ ሊያገኝ አልቻለም። በድርድር ሂደት ውስጥ ያሉት ኢትዮጵያና ሱዳን ተመሳሳይ የሆነ አቋም በመያዝ ለመፍትሄ ሲደክሙ ግብጽ ተለዋዋጭ አቋም በማንጸባረቅ ሂደቱ ወደውጤት እንዳያመራ እየጎተተችው ትገኛለች።

የናይል ውሃ ሳይነካ ግብጽ እንዲደርስ በመመኘቷም የወንዙን 80 በመቶ ውሃ የሚገብረው አባይ ምንጭ የሆነችው ኢትዮጵያ ሁልጊዜም ባይተዋር ሆና እንድትኖር ፍላጎት እንዳላት በተደጋጋሚ በምትገልጸው አቋሟ ላይ ታንጸባርቃለች። የግብጽ ፍላጎት ከህዳሴው ግድብ ግንባታ በፊትም ሆነ በኋላ የታየ ሲሆን በቅርቡ በተደረጉ ስምምነቶች ላይም ይህንኑ የሚያጠናክር ሀሳቧ ተደምጧል።

የኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን የውሃ ሚኒስትሮች አሜሪካ እና የዓለም ባንክ በታዛቢነት የተካፈሉበትን 4ኛ ዙር የቴክኒክ ውይይት ሲያጠናቅቁ ከግብፅ የቀረቡ አዳዲስ ሀሳቦች ውይይቱ ያለ ስምምነት እንዲጠናቀቅ ማስገደዱ ይታወሳል።

በቴክኒክ ውይይቶቹ ላይ ለረጅም ጊዜ የተካፈሉትና ለጉዳዩ እጅግ ቅርብ የሆኑት ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ ለተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እንደገለጹት፤ ግብፅ ኢትዮጵያ አቅርባው በነበረውን ግድቡን ከአራት እስከ ሰባት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ በውሃ የመሙላት ሃሳብ ለመቀበል መዘጋጀቷን የሚያሳይ የተለሳለሰ አቋም ይዛ ነበር።

ነገር ግን ‘አዲስ ጥናት አስጠንተናል’ በሚል ሰበብ ‘ግድቡ ከ12 እስከ 21 አመት ባለው ጊዜ መሞላት አለበት’ የሚል ሃሳብ ይዛ ብቅ ማለቷ ሂደቱን ወደፊት ከመሄድ ይልቅ ወደኋላ የሚጎትት ሊሆን መቻሉን ይገልጻሉ። ግብፅ በ4ኛው ዙር ስብሰባ ይዛ የመጣችው አዲስ ሀሳብ በድርድር ሂደቱ ከስምምነት ላይ ለመድረስ ዝግጁ አለመሆኗን በግልፅ ያሳየ እንደነበር የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በመግለጽ የዶክተር ያዕቆብን ሃሳብን ያጠናክራሉ።

እንዲህ እንዲህ በማለት የድርድር ሂደቱን ፈጥኖ እንዳይሄድ የምታደርገው ግብጽ ለድርድሩ ምቹ ሁኔታ እንድትፈጥርና የውሃ አጠቃቀሟን እንድታስተካክል የዘርፉ ምሁራን ይመክራሉ። ለናሽናል ኢንተረስት የሚጦምሩት የሃይልና የአየር ጸባይ ተመራማሪው ማይክል ግሪኮ ”ግብጽ የውሃ አጠቃቀሟን ማስተካከል ካልቻለች በናይል ዙሪያ የሚደረጉ ድርድሮች በቀላሉ መፍትሄ ማግኘት አይችሉም” ይላሉ።

ሶስቱ አገሮች ባለፈው ወር ዋሺንግተን ላይ በአሜሪካና የአለም ባንክ አደራዳሪነት በመሰባሰብ በግድቡ አሞላል ዙሪያ መፍትሄ ለማበጀት መክረዋል። ግብጽ በትንሹ ግድቡ በሰባት አመት መሞላት አለበት የሚል ሃሳብ ስታቀርብ ኢትዮጵያ በበኩሏ ከአምስት አመት በላይ ጊዜ እንደማትቀበል አሳውቃለች።

የህዳሴውን ግድብ ፍሬ ለመቅመስ ሌት ተቀን በትጋት እየሰራች የምትገኘው ኢትዮጵያ ከዚህ በላይ ጊዜ የመቀበል ፍላጎት እንደሌላት በተደጋጋሚ አሳውቃለች። ሁለት አመት ምንም ላይሆን ይችላል ነገር ግን በኢትዮጵያ መብራት የሚፈልጉ ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎችና የኢንዱስትሪ ፓርኮች የኤሌክትሪክ አቅርቦት ያስፈልጋቸዋል።

እንደ ማይክል ግሬኮ፤ የአገሮቹ ውይይት ባለፈው ወር ያለ ውጤት ቢጠናቀቅም የአገሮቹ ድርድር በስምምነት ሊጠናቀቅ የሚችልበት ዕድል ይኖራል። ነገር ግን ይህ እድል እውን ሊሆን የሚችለው ሁሉም ወገን ‘የእኔ ፍላጎት ብቻ ይፈጸም’ ከሚል ራስ ወዳድነት መላቀቅ ሲችል እንደሆነ ያስገነዝባሉ።

ሶስቱ አገሮች በአሜሪካና በአለም ባንክ አደዳሪነት ጉዳዩን ወደመቋጫው ለመውሰድ ቢንደረደሩም የሁሉንም ወገን ፍላጎት አሟልቶ መገኘት ባለመቻሉ ድርድሩ አሁንም ከጫፍ መድረስ አለመቻሉን በአሜሪካ የኢትዮጰያ አምባሳደር የሆኑት አቶ ፍጹም አረጋ በትዊተር ገጻቸው አስነብበዋል። የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ትናንት በሰጠው ሳምንታዊ ጋዜጣዊ መግለጫ መንግስት የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅም የማያስከብር ምንም ዓይነት ድርድር የማያካሂድ መሆኑን አረጋግጧል።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ ነቢያት ጌታቸው ”ከየትኛውም አካባቢ ተጽዕኖ ቢኖር፣ ባይኖር ኢትዮጵያ ራሷ የምትፈልገውን ከዚህ ቀደም ስታስቀምጠው በነበረው መርህ ላይ የተመሰረተ ድርድር ነው የምታካሂደው ያንን ውጤታማ በሆነ መልኩ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ይሄን መስመር ተከትለን እንደምንሄድ በተደጋጋሚ ተገልጿል፤ አሁንም ያንን አቅጣጫ የተከተለ አካሄድ ነው ያለው።” ብለዋል።

የአገሮቹ የውሃ ሚኒስትሮች ቀደም ብለው በጋራ እንዳስታወቁት “የግድቡ የውሃ አሞላል የጊዜ ሂደት ተቀምጦለታል፤ አሞላሉ ሁሉንም በሚጠቅም መንገድና የዝናቡን ሁኔታና የታችኛውን የተፋሰሱን አገሮች የውሃ ሃብት ታሳቢ ባደረገ መልኩ ይከናወናል።” በሚል ቢያስቀምጡም አቋሟን ወጥ ማድረግ ያልቻለችው ግብጽ የኢትዮጵያን የጋራ ተጠቃሚነት ፍላጎት የሚሞላ መስመር ውስጥ መግባት ፈተና ሆኖባታል።

አገሮቹ በጉዳዩ ዙሪያ ለመነጋገር ጥር 18 አና 19 ቀጠሮ ቢይዙም ስምምነት ላይ ባለመድረሳቸው የህግና የቴክኒክ ጉዳዮችን በተመለከተ በድጋሚ የካቲት 2 እና 3 ውይይት አድርገዋል። የግድቡ የሙሌት ጊዜ ለግብጽ ጠቃሚ ቢሆንም ለኢትዮጵያም የህልውና ጉዳይ መሆኑ መካድ የለበትም ።

በስምምነቱ መሰረት ኢትዮጵያ ግድቡን በክረምት ወቅት መሙላት እንደምትችል ተቀምጧል፤ አለፍ ሲልም እስከ መስከረም መዝለቅ እንደሚችል ታሳቢ ተደረጓል። ግድቡ ከኢትዮጵያ ባለፈ ለግብጽና ሱዳን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው የአደባባይ ምስጢር ነው።

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ከሚሰጠው ጥቅም በተጨማሪ ለተፋሰሱ ግርጌ አገሮችም ሆነ ለሌሎች አገሮች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንደሚያስገኝ ይታመናል፡፡ ግድቡ የሱዳንና የግብጽ ግድቦችን ከጎርፍና በደለል ከመሞላት ይታደጋቸዋል፡፡

በውሃ ኃብት ዙሪያ መረጃዎችን በየጊዜው የሚያወጣው aquapedia.waterdiplomacy.org የተሰኘው ድረ-ገጽ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በወንዙ ምክንያት በጎርፍ የሚጠቃውን መሬት በሁለት ሶስተኛ እንደሚቀንስ ያስቀምጣል። በተለይም በካርቱም አካባቢ የሚከሰተው ጎርፍ እንደሚቀንስና በወንዙ ዳር በሚገኘው አካባቢዎች ላይ የሚከሰተው ጎርፍ ሙሉ በሙሉ እንደሚወገድ አመልክቷል፡፡

መረጃው እ.ኤ.አ በ2013 በሱዳን ከ300ሺህ በላይ ህዝብን ለጉዳት የዳረገና የ25ሺህ ቤቶች ውድመት ያስከተለውን አስከፊ የጎርፍ አደጋ በማስታወስ፤ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ ተመሳሳይ የጎርፍ አደጋ ሊከሰት እንደሚችልና የሕዳሴው ግድብ ሱዳንን ከዚህ አደጋ ሊታደጋት የሚችል መሆኑን አስፍሯል፡፡

ወንዙ በበጋ ወቅት የተለመደ ፍሰቱን ይዞ ይቀጥላል። ነገር ግን ይህ ጉዳይ እስከምን ድረስ እንደሚዘልቅ ከሁሉም ወገኖች የተሰማ ነገር የለም። ነገር ግን የስምምነቱ የመጀመሪያ ደረጃ እንደሚያሳየው የህዳሴው ግድብ 595 ሜትር አካባቢ እንደሞላ የመጀመሪያው ዙር የሃይል ማመንጨት ሂደት ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል። ይህም የግብጽንና የሱዳንን የድርቅ ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ ሊያደርግ እንደሚችልም ተጠቅሷል።

አገሮቹ ድርቅ በሚከሰትበት ወቅት ችግሩን በጋራ ለመከላከል ሃላፊነቱን መውሰዳቸውም ተገልጿል። የድርቅ ችግር የጋራ ችግር በመሆኑ በተናጠል መቆጣጠር እንደማይቻልና የተፋሰሱን አገሮች የጋራ ትብብር እንደሚጠይቅ ይታወቃል። ከዚህ ባለፈ ችግሩን ለመቋቋም ሁሉም አገሮች የውሃ ሃብታቸውን በአግባቡ ለመጠቀም ቁርጠኛ መሆን ይጠበቅባቸዋል።

የህዳሴውን ግድብ ተከትሎ የተከሰተውን አለመግባባት ለመፍታት ግብጽ አገር አቀፍ ጥረቷን በመጠቀም የውሃ አጠቃቀም ዘዴዋን መከለስ አለባት። አሁን ላይ ግብጽ የውሃ ሃብቷን የምትጠቀመው ባልተጠና መልኩ እንደሆነ የሃይልና የአየር ጸባይ ተመራማሪው ማይክል ግሪኮ ይናገራሉ። ስለዚህ ግብጽ ገና ለገና የታላቁ የህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላል ‘ጥቅሜን ይነካል’ የሚል አቋም በመያዝ ‘እኔ ብቻ’ ከምትል የውሃ አጠቃቀሟን ማጤን እንዳለባት ምሁራኑ ያመለክታሉ።

የላይኛው የተፋሰሱ አገሮች የውሃ ፍላጎት እየጨመረ ሲመጣ የታችኛው የተፋሰሱ አገሮች ጭራሽ በውሃው አትጠቀሙ ከሚል አቋም ወጥተው ፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀም እውን የሚሆንበትን ሁኔታ ማሰብ ይጠበቅባቸዋል። ከዚህም ባለፈ ደግሞ በላይኛው የተፋሰስ አገሮች የአየር ንብረት ለውጥ እንዳይከሰት የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃን ማገዝ ይኖርባቸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የውሃ ፍጆታ ሁኔታውን መፈተሽ ይገባል። በዚህ ሂደት በቅድሚያ የሚጎዳው የግብርና ዘርፉ ሲሆን ግብርናው ከግብጽ የውሃ ሃብት ፍጆታ 79 ነጥብ 6 በመቶ ድርሻን ይዟል። ይህ ምጣኔ የግብጽን የታዳሽ ውሃ ሃብት 107 በመቶ ድርሻ ይዟል። በሌላ አገላለጽ የግብጽ የግብርና ዘርፍ የሚጠቀመው የውሃ ምጣኔ ወደ አገሪቱ ከሚገባው አመታዊ የውሃ ድርሻ እጅግ የላቀ ነው።

ይህንን እውነታ ማሻሻል ለግብጽ የማይቻል ቢመስልም ግዴታ መሆኑ ግን አይካድም። ነገር ግን የአገር ውስጥ የግብርና ዘርፉን አሰራር ማሻሻል የውሃ እጥረት የሚከሰትበትን ሁኔታ ለመቋቋም የማይተካ ሚና እንዳለው አይካድም። ማሻሻያው ደግሞ ማጠንጠን ያለበት በመስኖ ልማቱ ላይ ነው። እኤአ በ2010 በተደረገ ጥናት ከግብጽ የመስኖ እርሻ 82 ነጥብ 66 በመቶ በጎርፍ የመስኖ ዘዴ የሚታረስ ነው።

በዚህ የተነሳ በጎርፍ ከሚፈሰው ውሃ አብዛኛው ያለጥቅም የሚባከን ነው። ይህን የመስኖ አሰራር በግፊት የውሃ አጠቃቀም ወይም ውሃን በመርጨትና፣ በጠብታ ዘዴ በቀጥታ ለተክሎቹ እንዲደርስ በማድረግ ውሃን በእጅጉ መቆጠብ እንደሚቻል የዘርፉ ምሁራን ይመክራሉ።

እኤአ በ2018 በአለም ባንክ ድጋፍ በግብጽ የተከናወነው ዘመናዊ የመስኖ እርሻ ፕሮጀክት ትግበራ ውጤታማ በሆነ መልኩ በግብርናው መስክ የሚታየውን የውሃ ብክነት ማስቀረት ችሏል። በፕሮጀክቱ በናይል ዴልታ አካባቢ 105 ሺህ ሄክታር መሬት ማልማት ተችሏል።

በፕሮጀክቱ ከዚህ በፊት የአካባቢው ነዋሪዎች ከሚጠቀሙት የውሃ ፍጆታ 18 በመቶ መቀነስ የተቻለ ሲሆን የግብርናውን ምርታማነት በ10 በመቶ ከፍ እንዲል አድርጎታል። የግብጽ መንግስትም ተጨማሪ 2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ከማልማቱ በፊት የመስኖ አተገባበሩን የቴክኒክ ዲዛይንና አዋጪነቱን መከለስ ተገቢነት አለው።

ግብጽም 5 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር የመደበችለትና 12 አመት ይፈጃል የተባለው የመስኖ ልማት ስኬታማ እንዲሆን ዘመናዊ የመስኖ አጠቃቀምን መከተል አለባት። ወጪው ከፍተኛ ቢመስልም በጊዜ ሂደት የሚገኘው ውጤት ግን የላቀ መሆኑ አያጠያይቅም። በተለይ የአየር ፀባይ ለውጥ ተለዋዋጭ በሚሆንበት ጊዜና፣ የደመና መጠኑና የናይል ፍሰት በሚቀንስበት ወቅት ጠቀሜታው የጎላ ነው።

በአሌክሳንዳሪያ ዩኒቨርሲቲ የሃይድሮሎጂ ምሁር የሆኑት ፕሮፌሰር ሀተም አዋድ በአስዋን ግድብ ላይ የተገነባው ሰው ሰራሽ የግድቡ ውሃ ማቆሪያ የሆነው የናስር ሃይቅ ውስጥ ከሚከማቸው ውሃ ውስጥ 12 በመቶ በትነት እንደሚባክን ይናገራሉ። በተለይም በነሓሴ መጨረሻና መስከረም ወር መጀመሪያ አካባቢ ወደ ሃይቁ የሚገባው ከፍተኛ መጠን ያለው ውሃ ለትነት እንደሚዳረግና ውሃውን በሕዳሴ ግድብ ማቆር መፍትሄ እንደሚሆን ይጠቅሳሉ፡፡

ይህም አስዋን ግድብ የሚደርሰውን የውሃ መጠን በየዓመቱ በአምስት በመቶ እንዲጨምር ያደርጋል፡፡ በተጨማሪም ግድቡ በደረቃማ ወቅት ላይ የውሃውን አነስተኛ የፍሰት መጠንን በማስተካከል ካርቱም የሚደርሰውን ውሃ በአምስት እጥፍ እንዲጨምር ይረዳል፡፡

በመሆኑም ግብጽ የህዳሴውን ግድብ እንደስጋት በማየት ከያዘችው አቋሟ በመውጣት ስጋቱን ወደ እድል በመቀየር የጋራ ተጠቃሚነትን ማለም ይገባታል በሚል ምሁራኑ ይጠቁማሉ። በዋናነት የውሃ አጠቃቀም ልማዷን መፈተሽ ወሳኝ እንደሆነም ያስቀምጣሉ። ስለዚህ ግብጽ የናይል ውሃን በተመለከተ አሻግራ ማዶ ያለውን የኢትዮጵያን በረከቷን እንደ ስጋት ከማየት ወጥታ በጉያዋ ያለውን የውሃ ብክነት ምንጭ ማድረቅ እንዳለባት ይመከራል።