ላሞቻቸውን የውጭ ዝርያ ካላቸው ኮርማዎች ጋር በማዳቀል ተጠቃሚ መሆናቸውን አርሶ አደሮቹ ተናገሩ

144
ባህርዳር ኢዜአ የካቲት 07/2012 ፡- በባህላዊ መንገድ የሚያረቧቸውን ላሞች የውጭ ዝርያ ካላቸው ኮርማዎች ጋር በማዳቀል ተጠቃሚ መሆናቸውን በአማራ ክልል የምዕራብ ጎጃም ዞን አርሶ አደሮች ተናገሩ። በክልሉም ባለፉት ስድስት ወራት 125 ሺህ የሚጠጉ ላሞችን በማዳቀል የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ መሰራቱ ተመልክቷል። በምዕራብ ጎጃም ዞን ሰሜን ሜጫ ወረዳ የእንጉቲ ቀበሌ አርሶ አደር ሙሉ ብርሃን ለኢዜአ እንደገለጹት ባለፉት ስምንት ዓመታት ላሞቻቸውን ከተሻሻሉ የውጭ ዝርያዎች ጋር በማዳቀል ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። ከዚህ በፊት በባህላዊ መንገድ ያረቧቸው የነበሩ ሶስት ላሞችን በማዳቀል ከወለዱላቸው ስምንት ጥጆች ውስጥ  አራቱን ከ33 ሺህ ብር በላይ በመሸጥ ለቤት ፍጆታና ቁጠባ ማዋል ችለዋል። ከጥጆቹ ሽያጭ በተጨማሪም በቀን  የወተት ምርት ከአንድ ሊትር ተኩል ወደ  14 ሊትር በማሳደግ ከሽያጩ በወር ስድስት ሺህ ብር የሚጠጋ ገቢ እንደሚያገኙ ተናግረዋል። በዚሁ ወረዳ የእናምርት ቀበሌ አርሶ አደር አስማማው ወርቁ በበኩላቸው ሁለት የተዳቀሉ ጊደሮችን ከቻግኒ የዳልጋ ከብት ዝርያ ማሻሻያና ጥበቃ ማዕከል በ10 ሺህ ብር በመግዛት ዘመናዊ እርባታ ከጀመሩ አራት ዓመት እንደሆናቸው ገልጸዋል። አሁን ላይ ቁጥራቸውን አምስት ከማድረስ ባሻገር ወተት ከሚሰጡ ሁለት ላሞቻቸው በየቀኑ 24 ሊትር ወተት በማግኘት የወር ገቢያቸውን ከ11ሺህ ብር በላይ አድርሰዋል። ሌላኛው አርሶ አደር አዲሴ ከበደ እንዳሉት ተጠቃሚ የሆኑ የአካባቢው አርሶ አደሮችን ለውጥ በማየት ባለፈው ህዳር ወር ላይ ያሏቸውን ሶስት የአካባቢ ላሞች አዳቅለዋል። ወደ ዘመናዊ የእንስሳት እርባታ እንዲገቡም የቀበሌና የወረዳ የእንስሳት ባለሙያዎች የተጠናከረ ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርጉላቸው አርሶ አደሮቹ ተናግረዋል። በአማራ ክልል እንስሳት ሃብት ልማት ማስፋፊያ ኤጀንሲ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ባለሙያ አቶ አህመድ አልቃድር በበኩላቸው የእንስሳት ዝርያን በማሻሻል የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት 125 ሺህ የሚጠጉ ላሞችን የውጭ ዝርያ ካላቸው ጋር ማዳቀል እንደቻሉ አመልክተዋል። "የአካባቢ ላሞች በአማካይ የሚሰጡትን ከሁለት ሊትር በታች የወተት ምርት ዝርያቸውን በማሻሻል ወደ 12 ሊትር ወተት ማሳደግ በመቻሉም የአርሶ አደሩ ተጠቃሚነት እንዲያድግ አስችሏል "ብለዋል። በቀሪው ግማሽ የበጀት ዓመትም ከ249 ሺህ በላይ ላሞችን ለማዳቀል ታቅዷል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም