ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሻለ የሰብዓዊ መብት አያያዝ እንድናገኝ አድርገውልናል ....በመካከለኛው ምስራቅ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን

94

አዲስ አበባ፤ የካቲት 7/2012 (ኢዜአ ) ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደ ኃላፊነት ከመጡ በኋላ የሚደረግላቸው የሰብዓዊ መብት አያያዝ መሻሻሉን ኢዜአ ያነጋገራቸው በመካከለኛው ምስራቅ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ገለጹ።

በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ይፋዊ የስራ ጉብኝት ላይ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመካከለኛው ምስራቅ አገራት ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ትናንት በሸባብ አላሕሊ ስታዲየም ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው ከብልጽግና እሳቤ ምሰሶዎች አንዱ የዜጎች ክብር መሆኑን ተናግረዋል።

መንግስት ይህን በመረዳት በተለይ በመካከለኛው ምስራቅ አገራት የሚኖሩ ዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ ከአገራቱ ጋር ሰፊ የዲፕሎማሲ ስራ ሰርቷል ነው ያሉት።

በመሪዎች ደረጃ ከሚሰራው የዲፕሎማሲ ስራ በተጓዳኝ በአካባቢው የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ለዜጎች ትኩረት እንዲሰጡ አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ኢዜአ በአካባቢው የሚኖሩ ዜጎች ወቅታዊ ሁኔታ ምን እንደሚመስል በስታዲየሙ የታደሙ ኢትዮጵያዊያንን አነጋግሯል።

በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች አቡዳቢ ከተማ የምትኖረው ሰላማዊት ታደሰ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደ ኃላፊነት ከመጡ በኋላ 'በምንኖርበት አካባቢ የሚሰጠን ክብር እጅጉን ተሻሽሏል' ትላለች።

አሁን ላይ "ኢትዮጵያዊነት ክብር መሆኑን ተገንዝቤያለሁ" ስትል ተናግራለች።

በዱባይ የሚኖሩት አቶ አብዱረሺድ ጀማል በበኩላቸው ከዚህ ቀደም በሚኖሩበት አገር የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በተገቢው መልኩ አገልግሎት ሲሰጣቸው እንዳልነበረ አስታውሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ኃላፊነት ከመጡ በኋላ ግን ችግሩ እንደተፈታ ነው የገለጹት።

በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሠላም ኖቤል ሽልማት ማሸነፋቸው በምንንቀሳቀስበት ቦታ ሁሉ ክብር እንድንጎናጸፍ አድርጎናል ብለዋል።

ሕጋዊ ሰነድን ያሟሉትን ጨምሮ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በእንግልት የተሞላ ነበር ያሉት ደግሞ በሳዑዲ ዓረቢያ ጂዳ የሚኖሩት አብዱላሂ ሃሰን ናቸው።

አሁን ችግሩ በመቀረፉ ያለምንም እንግልት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት ሁነት ላይ መታደም ችያለሁ ብለዋል።

መንግስት ዜጎቹን በሚለከት እያከናወነ ያለውን ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በቆይታቸው ከመካከለኛው ምስራቅ አገራት ከተውጣጡ ኢትዮጵያዊያን ሴቶች ጋር እንደሚመክሩም ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም