ምርጫ ቦርድ ህግና ስርዓት የማስከበርና የ'አባላቶቼ ታሰሩብኝ' የሚሉ አቤቱታዎችን ጉዳይ በጥንቃቄ እንዲያይ ተጠየቀ

54
አዲስ አበባ፣ 6/2012 (ኢዜአ) የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ህግና ስርዓት ማስከበርና የ'አባላቶቼ ታሰሩብኝ' የሚሉ አቤቱታዎችን ጉዳይ በጥንቃቄ ሊያየው እንደሚገባ ተገለፀ። ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሁለተኛውን የምርጫ ባለድርሻ አካላት ኮንፈረንስ ዛሬ አካሂዷል። በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሙሳ አደም እንዳሉት፤ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን የማሰር፣ የማስፈራራትና የማሸማቀቅ ተግባር እየተፈፀመ ነው። በተጨማሪም የፓርቲ አርማና ስም ማስታወቂያ ቦርድ የመንቀል ተግባር መፈፀሙን ፓርቲዎች እያሳወቁ መሆኑን ጠቅሰዋል። የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ቀጄላ መርዳሳ በበኩላቸው የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ላይ የሚደረገው እስር አሳሳቢና በመጪው ምርጫም ለሚደረጉ ዝግጅቶች ዋነኛ እንቅፋት መሆኑን ተናግረዋል። የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በዚህ ዙሪያ ሊሰራ እንደሚገባም የፓርቲ ኃላፊዎቹ ገልፀዋል። የብልፅግና ፓርቲ አመራር ዶክተር አለሙ ስሜ ደግሞ ህግና ስርዓት የማስከበርና የ'አባላት ታሰሩብኝ' አቤቱታን ቦርዱ እንዴት በጥንቃቄ ያየዋል የሚል ጥያቄን አንስተዋል። በተለያዩ ቦታዎች የህግ ጥሰቶችና የሰላም እጦት እየተስተዋሉ መሆናቸውንና አንዳንዴም የፖለቲካ ፓርቲዎች ራሳቸው በኢ-መደበኛ አደረጃጀት በነፃነት መንቀሳቀስ የማይችሉበት ሁኔታ እየተፈጠረ መሆኑን አንስተዋል። ''ይህ ችግር ምርጫውን በሰላምና በዲሞክራሲያዊ መንገድ ለማካሄድ ተግዳሮት ሆኗል'' በማለት ገልጸው፤ መንግስትም ይህን ለማስተካከል ጠንካራ ህጋዊ እርምጃ እንዲወስድ የህዝብና የሁሉም አካላት ጥያቄ እንዳለ ገልጸዋል። ሰላምን የሚያውኩ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ደጋፊዎቻቸው ችግር ፈጥረው ህጋዊ እርምጃ ሲወሰድ 'አባሎቼ ታሰሩብኝ' በሚል አቤቱታው የሚያቀርቡ ፓርቲዎች ጉዳይ በጥንቃቄ መታየት እንዳለበት አስገንዝበዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎች ኢ-መደበኛ አደረጃጀት እየተጠቀሙ በሰላምና በነፃነት መንቀሳቀስን እያወኩ እንደሆነ የገለጹት ዶክተር ዓለሙ፤ ''መንግስት እርምጃ መውሰድ ሲጀምር አባላት ታሰሩብኝ አቤቱታዎች ከበዙ ህግና ስርዓትን አስከብሮ ምቹ የፖለቲካ ሜዳ የመፈጠር ቁርጠኝነትን አያዳክምም ወይ'' የሚል ጥያቄ እንዳላቸው ገልጸዋል። ቦርዱ እንደገለፀው፤ ከ12 የፖለቲካ ፓርቲዎች በአባሎቻቸውና በአመራሮቻቸው ላይ ጉዳትና እስር እየገጠማቸው እንደሆነ በመግለጽ አቤቱታ አቅርበዋል። የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ እንዳሉት፤ ቦርዱ ባለፉት ወራት መሰል ችግሮችን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር አበረታች ውጤት ማምጣት ተችሏል። ቦርዱ በተለያየ መንገድ አቤቱታዎችን እያስተናገደና እየመረመረ እንደሆነም ገልፀዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም