በኢትዮጵያውያን የተነደፉ አምስት የፈጠራ ስራዎች በቻይና ሊመረቱ ነው

161
አዲስ አበባ ሰኔ 20/2010 በኢትዮጵያውያን የተሰሩ አምስት የፈጠራ ንድፎች በቻይና ወደ ምርት ሊሸጋገሩ መሆኑን  አስታወቀ። ምርቶቹ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ናቸው ተብሏል። ሚኒስቴሩ “በኢትዮጵያ የተነደፈ'' ተብሎ በሚጠራው ፕሮጀክት አማካኝነት 100 የፈጠራ ሥራዎችን በምርት ጥራታቸው፣ በጠቀሜታቸው እና በገበያ ተፈላጊነታቸው መሰረት በማወዳደር የተሻሉ የተባሉትን አምስቱን መርጦ ወደ ምርት እንዲሸጋገሩ ማዘጋጀቱን ገልጿል። ለምርት ከተዘጋጁት ፈጠራዎች መካከል አንዱ ዓይነ ስውራን በፈለጉት ቋንቋ በድምፅ መልዕክት ማተላለፍ የሚያስችለው “ስማርት ኬን” እና “ስማርት መነፅር” ነው። ኤፍ ኤም ሬዲዮ በማያጫውቱ ኮምፒውተሮች ላይ ሬዲዮ ለማዳመጥና ድምጽ ለመቅዳት የሚያግዝ ቁስና የህመምተኞችን የሰውነት ድምፅ አጉልቶ የሚያሰማና ድምፅ የሚቀዳ መሳሪያም ሌሎቹ ወደ ምርት እንዲሸጋገሩ የተመረጡ የፈጠራ ሥራዎች ናቸው። ከዚህም ሌላ የኤሌክትሮኒክ ቦርድ እና የቤት ውስጥ የፀሀይ ኃይል መጠቀሚያዎችን ጨምሮ  መብራቶችንና በሮችን በአውቶማቲክ ስርዓት ለመቆጣጠር የሚያስችሉ መሳሪያዎችም ሌሎቹ ለአገልግሎት እንዲበቁ የተመረጡ ፈጠራዎች መሆናቸውም ተመልክቷል። በሚኒስቴሩ የቴክኖሎጂ ሽግግርና ልማት ጉዳዮች ዳይሬክተር ዶክተር ኻሊድ አህመድ እንደገለፁት የፈጠራ ሥራዎቹ በመጪው ቅዳሜ ይፋዊ እውቅና ይሰጣቸዋል። ከእውቅናው በኋላም በቻይና ሸንዘን ኢኮ ሲስተም ኩባንያ ወደምርት ተሸጋግረው ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ዝግጁ ይደረጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። የፈጠራ ሥራዎቹ ወደ ምርት መሸጋገራቸው የተጠቀሱትን ችግሮች ከመፍታት ባሻገር ለዓለም ገበያ ቀርበው የኢትዮጵያን ሥም ያስተዋውቃሉ፤  የፈጠራ ባለቤቶቹም  ለሌላ ፈጠራ አንዲነሳሱ ያበረታታቸዋል ሲሉ አቶ ኻሊድ ገልፀዋል። "በኢትዮጵያ የተነደፈ" ፕሮጀክት በቀጣይም ተመሳሳይ የውድድር መድረክ አዘጋጅቶ የፈጠራ ሥራዎችን እንደሚመርጥ አስታውቀዋል። የፈጠራ ባለቤቶቹ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በሰጣቸው እድል በመወዳደራቸው ፈጠራቸውን ማስተዋወቅ እንደቻሉና ወደ ፊትም ምርቶቻቸውን ከዘመኑ ጋር ለማሻሻል ተጨማሪ ምርምሮችን እንዲያደርጉ እንደሚያበረታታቸው ገልፀዋል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም