ኢጋድ የኢትዮ-ኤርትራን የሰላም ጅምር አደነቀ

86
አዲስ አበባ ሰኔ 20/2010 የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን /ኢጋድ/ ኢትዮጵያና ኤርትራ የጀመሩትን የሰላም ድርድር አደነቀ። የኢጋድ ዋና ጸሃፊ አምባሳደር ኢንጂነር ማህቡብ ማሊም የኤርትራ ከፍተኛ ልዑካን ለውይይት አዲስ አበባ መግባታቸውን አሞካሽተዋል። ይህም የሁለቱ አገራት ግንኙነት ከተቋረጠ ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ የመጀመሪያ መሆኑን በመጠቆም። ˝አምባሳደር˝ ማሊም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የአገራቱን አለመግባባት በሰላም ለመፍታት ለነበራቸው ተነሳሽነት ምስጋና አቅርበዋል። የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ በአዎንታ መቀበላቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል። በሁለቱ አገራት መካከል የሚካሄደው ውይይት ለአገራቱ፤ እንዲሁም ለቀጣናው ፍሬ ያፈራል የሚል ግምት አለኝ ብለዋል። ለዚህም ኢጋድ የበኩሉን ድርሻ እንደሚያደርግ ነው ያረጋገጡት። አምባሳደሩ በሰላሙ ውጤት ተጠቃሚ ለሚሆኑት የሁለቱ አገራት ሕዝቦች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ኢጋድ ለኢዜአ በላከው መረጃ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም