አገራቸውን ወክለው በተለያዩ ውድድሮች ላሸነፉ አትሌቶች የማበረታቻ ሽልማት ተሰጠ

63
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 6/2012 መንግስት አገራቸውን ወክለው በተለያዩ ዓለምና አህጉር አቀፍ ውድድሮች ውጤት ላስመዘገቡ አትሌቶችና የልዑካን ቡድን አባላት የማበረታቻ ሽልማት ሰጠ። አንዳንድ አትሌቶች ስለ ሽልማት አሰጣጡ የተሰማቸውን ቅሬታ ለኢዜአ ገልጸዋል። ትናንት ምሽት በአዲስ አበባ ለተሰጠው ሽልማት መንግስት ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉም ተነግሯል። ሽልማቱ የተበረከተው ካለፈው ዓመት ጀምሮ በተለያዩ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ውድድሮች አገራቸውን ወክለው ለተሳተፉ አትሌቶችና ልዑካን ቡድን አባላት ነው። የ17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና፣ የ12ኛው የመላ አፍሪካ ጨዋታ፣ የ6ኛው የአፍሪካ ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ሻምፒዮና፣ በአፍሪካ መስማት የተሳናቸው አትሌቲክስ ሻምፒዮናና በምስራቅ አፍሪካ ጠረጴዛ ቴንስ ውደድሮች የተሳተፉ የልዑካን ቡድን አባላት በሸልማቱ ተካተዋል። የተበረከተው ሸልማት ስፖርተኞቹ እንዳመጡት ውጤትና እንደ ውድድሩ ዓይነት ከ5 ሺህ እስከ 80 ሺህ ብር የሚደርስ ሸልማት ለስፖርተኞች፣ ለአሰልጣኞች፣ ለሀኪሞችና ለልዑካን ቡድን አባላት ተሰጥቷል። በዚሁ መሰረት ከፍተኛውን የገንዘብ ሽልማት ያገኙት በ17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተካፈሉ የልዑካን ቡድን አባላት ናቸው። በአትሌቲክስ ሻምፒዮናው የወርቅ ሜዳሊያ ላመጡ አትሌቶች 80 ሺህ፣ ብር ላመጡ 60 ሺህ እና የነሐስ ሜዳሊያ ላስገኙ ደግሞ 40 ሺህ ብር ተበርክቶላቸዋል። በመላ አፍሪካ ጨዋታዎች ተካፍለው የወርቅ ሜዳሊያ ያመጡ ስፖርተኞች ደግሞ 40 ሺህ፣ የብር ሜዳሊያ ላመጡ 30 ሺህ የነሐስ ሜዳሊያ ያስገኙም 20 ሺህ ብር ተሸልመዋል። በሌሎች ውድድሮች የተካፈሉ አትሌቶችም የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። በዚህ ሸልማት የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ ለስፖርቱ እድገት እያበረከቱት ላለው አስተዋጽኦ ልዩ ተሸላሚ ሆነዋል። ኢዜአ የሽልማት ስነ-ስርዓቱን ተከትሎ ያነጋገራቸው አንዳንድ አትሌቶች ስለ ሽልማቱ ያላቸውን ቅሬታ ገልጸዋል። በ17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ5 ሺህ ሜትር ለአገሩ የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኘው አትሌት ሙክታር እንድሪስ አትሌቲክስ ብዙ ተለፍቶበት የሚገኝ ውጤት ነው ይላል። በመሆኑም አትሌቶች ብዙ ነገር ባልተሟላበት ሁኔታ በጥረታቸው ለሚያመጡት ውጤት ተገቢው እውቅናና ሽልማት ሊሰጥ ይገባል ሲልም ተናግሯል። ሽልማቱ መሰጠት ያለበት በሆቴል ሳይሆን "በብሔራዊ ቤተመንግስት" ሊሆን ይገባል ሲልም ገልጿል። በኳታር ዶሃ 17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ10 ሺህ ሜትር የብር ሜዳሊያ ያመጣው አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻም "ለምን ብዙ አትሌቶች ሽልማቱ ላይ መገኘት እንዳልፈለጉ በራሱ የሚናገረው ነገር አለ" ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል። በሽልማት መርሃ ግብሩ ላይ አንዳንድ አትሌቶችን ጨምሮ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት አትሌት ደራርቱ ቱሉና የፌዴሬሽኑ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ አልተገኙም። በኳታሩ የዓለም ሻምፒዮና የ3 ሺህ ሜትር መሰናክል ሩጫ በአራተኝነት ያጠናቀቀው አትሌት ጌትነት ዋለ አገርን ወክሎ መወዳደር በምንም የማይተካ ትልቅ ደስታ እንደሚሰጥና የአትሌቲክስ ስፖርት ብዙ ልፋትና ውጣውረድ እንዳለው ገልጿል። ስለሆነም በዚህ ውጣውረድ አልፈው የአገራቸውን ሰንደቅ ዓላማ ለሚያውለበልቡ አትሌቶች ከዚህ በበለጠ ተገቢውን ክብር በመስጠት መሸለምና ማበረታታት ይገባል ብሏል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም