ከጊዜ ጋር የሚሽቀዳደመው...  

82

ሰለሞን ተሰራ/ኢዜአ/

ዓለማችን የሰው ልጆችን ህይወት በፍጥነት የሚቀጥፉ በርካታ ገዳይ በሽታዎችን በተደጋጋሚ አስተናግዳለች።

ከነዚህ በሽታዎች ውስጥ የኮሌራ ወረርሽኝና በቅርቡ ደግሞ ኤችአይቪ/ኤድስ፣ ሳርስና ኢቦላ የሚጠቀሱ ሲሆኑ፤ ከነዚህ ውስጥ ኤድስ የአጥቂነቱ ዕድሜ እየተራዘመ ሲሔድ ሌሎቹን ግን መቆጣጠር ተችሏል።

በቅርቡ ደግሞ በቻይና ሁቤይ ግዛት ዉሃን ከተማ የተነሳው የኮሮናቫይረስ በትንፋሽ እንደሚተላለፍ የተነገረለት ሲሆን፤ በቀላሉ የሚዛመት በመኾኑ ለብዙ አገሮች ሥጋት ሆኗል።

በሽታው በተገኘባት ቻይና ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች ሲሞቱ፤ ቻይናን ጨምሮ በተለያዩ አገሮች 60 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ደግሞ በበሽታው መያዛቸው እየተነገረ ነው።

የዓለም ጤና ድርጅትም የኖቭል ኮሮናቫይረስ በሽታ ከታሕሳስ 21 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በዉሃን ከተማ መከሰቱን ተከትሎ 'የአለም የጤና ስጋት' ሲል ፈርጆታል።

ይህ ቫይረስ ቀደም ብሎ የሚታወቅ በሽታ አምጭ ተኅዋስ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት የተከሰተው ግን አዲስ የቫይረስ ዓይነት እንደሆነ መገለጹም ይታወሳል።

የበሽታውን መከሰት በተመለከተ የሙያ አጋሮቹ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ሲመክር የነበረ አንድ የቻይና ሐኪም ፖሊሶች ቤቱ ድረስ መጥተው ከድርጊቱ እንዲቆጠብ ማስጠንቀቃቸውና በመንግስት አፋጣኝ ርምጃ መወሰድ አለመቻሉ ቀውሱን እንዳባባሰው ተነግሯል።

ከአንድ ወር በኋላም በሽታው በወረርሽኝ መልክ ተከስቶ ዓለምን ማስጨነቅ ሲጀምር ሐኪሙ ጀግና ተብሎ የተወደሰ ቢሆንም በዚህ ሳምንት በቫይረሱ ምክንያት ህይወቱ ሊያልፍ ችሏል።።

ዶክተሩ ይፋ ያደረገው መልዕክት የኮሮናቫይረስ በተከሰተባቸው የመጀመሪያ ሳምንታት ዉሃን ውስጥ ያሉ ባለስልጣናት በሽታውን ለመሸፋፈን ያደረጉትን ጥረት ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ነው ተብሏል።

ወረርሽኙ በተከሰተበት ማዕከል ውስጥ ይሰራ የነበረው ዶክተር ሊ በአንድ እንግዳ ቫይረስ ተጠቅተው የመጡ ሰባት ሰዎችን አግኝተው ነበር፤ እሱም በሽታው ከዓመታት በፊት ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ሆኖ የነበረው 'ሳርስ' ነው ብሎ ገምቶ እንደነበርም ነው የተነገረው።

በቻይና በመጀመሪያ የበሽታው ምልክት የታየው በውሃን ከተማ የባሕር ምግቦችን በሚያዘጋጁና በሚያቀርቡ ሰዎች ላይ ሲሆን  ወደ አሜሪካ፣ ጃፓን፣ ታይላንድ፣ ኮሪያ ሪፐብሊክ እና ሲንጋፖር ከቻይና በተነሱ ተጓዦች አማካኝነት መሰራጨቱ ታውቋል፡፡

እስካሁን አፍሪካ ውስጥ ቫይረሱ ባይከሰትም  ቢከሰት ግን ሁኔታዎች አዳጋች ሊሆኑ እንደሚችል እየተገመተ ነው።

ያም ሆኖ ግን ችግሩን አስቀድሞ ለመከላከል ከወዲሁ ዝግጅት መደረጉን ከሰሞኑ ሲካሄድ በነበረው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ  ተገልጿል።

በሴኔጋልና በደቡብ አፍሪካ ብቻ የነበረውን የኮሮናቫይረስ መለያ ቤተ ሙከራ አገልግሎት በዚህ ሳምንት ኢትዮጵያን ጨምሮ ጋና፣ ማዳጋስከር፣ ናይጄሪያና ሴራሊዮን አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል።

የዓለም ጤና ድርጅትም በአህጉሩ ያሉ 29 ቤተ ሙከራዎች ቫይረሱን መለየት እንዲችሉ ድጋፍ ለማድረግ አጋዥ ቁሳቁስ የላከ ሲሆን አስፈላጊ ከሆነ ከሌሎች አገሮች ተጨማሪ ድጋፍ ለማምጣት መዘጋጀቱን ገልጿል።

በመቀጠልም በዚህ ወር መጨረሻ ቢያንስ 36 የአፍሪካ አገሮች የኮሮናቫይረስን ለመለየት የሚያስችል ቤተ ሙከራ ይኖራቸዋል ተብሎ ተስፋ ተደርጓል።

ለዚህም ቫይረሱ ከመሰራጨቱ በፊት ከፍተኛ የሆነ የመለየት ሥራ ላይ አገሮች እንዲረባረቡ የአለም ጤና ድርጅት ይመክራል።

የኮሮና ቫይረስ ከቀላል እስከ ከባድ የመተንፈሻ አካል ሕመም የሚያስከትል የቫይረስ ዝርያ ሲሆን በበሽታው የተያዙ ሰዎች ትኩሳት፣ ሳል፣ የትንፋሽ መቆራረጥና የመተንፈስ ችግር ምልክቶች ይታይባቸዋል፡፡

በሽታው በጠናባቸው ታማሚዎች ላይ የሳንባ ምችና ከባድ የመተንፈሻ አካላት ሕመም የሚያስከትል ሲሆን የኩላሊት ስራን በማወክ ሞትን ሊያስከትል እንደሚችል እየተደረጉ ያሉ የምርምር ግኝቶች አሳይተዋል ፡፡

በሽታው ባልበሰሉ ምግቦች፣ በሳልና በማስነጠስ ወቅትና ከታማሚ ሰው ጋር በሚደረግ የቅርብ ንክኪ፣ እንደሚተላለፍ የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ሳይንስ ኢንስቲቲዩት መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቻይና ብቻ ወደ ቤጂንግ፣ ሆንግ ኮንግ፣ ሻንግሃይ፣ ቸንዱና ጓንዡ በረራዎችን ያደርጋል፡፡

በመሆኑም ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡም ሆነ ከኢትዮጵያ የሚወጡ መንገደኞች ለቫይረሱ ተጋላጭ እንዳይሆኑ በሽታውን የተመለከተ መረጃ መስጠትና ወደ ኢትዮጵያ ለሚገቡት ደግሞ በአለም የጤና ድርጅት ምክረ ሀሳብ መሰረት ለሁሉም መንገደኞች የሰውነት ሙቀት ልየታ ስራ በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ተጀምሯል፡፡

ወደ ውጭ በተለይም በሽታው ወደ ተከሰተባቸው አካባቢዎች ከተጓዙ ትኩሳትና የሳል ምልክት ከሚያሳዩ ሰዎች ጋር ንክኪ አለማድረግ፣ በተለይ ደግሞ ከታመሙ ሰዎች ወይም ከአካባቢያቸው ጋር ንክኪ ከፈጠሩ እጅን በሳሙናና ውሃ መታጠብ፣ ያልበሰሉ የእንስሳት ተዋጽኦዎችን አለመመገብ፣ በሕይወት ካሉም ሆነ ከሞቱ የቤትና የዱር እንስሳት ጋር ንክኪ አለማድረግ ይበጃል ተብሏል።

ቸር ያሰማን!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም