በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተጀመረው አዲስ የግንኙነት ምዕራፍ የሚደነቅ ነው-ሱዳን

59
ሰኔ 20/2010 ሱዳን በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተጀመረው አዲስ የግንኙነት ምዕራፍ የሚደነቅ መሆኑን ገለፀች፡፡ ኤርትራ የልዑካን ቡድኗን ወደ አዲስ አበባ መላኳን ተከትሎ ነው ሱዳን የሁለቱን ሀገራት አዲስ የግንኙነት ምዕራፍ የሚበረታታ ነው ያለችው፡፡ የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ በሀገሪቱ ሁለት አጎራባች ሀገራት በኩል ለተጀመረው የመልካም ግንኙነት ምዕራፍ ከፍተኛ አድናቆት አለን ብሏል፡፡ ሁለቱ ሀገራት ለዓመታት ሻክሮ የቆየውን ግንኙነታቸውን በመሻር የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች ፈላጎት እንደሚያስጠበቁ እምነት አለኝ ብላለች፡፡ በቀጠናው ፀጥታና መረጋጋት እንዲፈጠር ሁለቱም ሀገራት እንደሚግባቡ ተስፋ እንዳላት ነው ሱዳን የገለፀችው፡፡ ሱዳን ቀጠናዊ የኢኮኖሚ አደረጃጀት እንዲፈጠርና ኢትዮጵያና ኤርትራን ጨምሮ በሶስቱ ሀገራት ህዝቦች መካከል የንግድ ትስስር እንዲኖር ድንበሯን ክፍት የማድረግ ፍላጎት አላት፡፡ በኤርትራው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኦስማን ሳሊሕ እና በፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ አማካሪ የማነ ገበረአብ የተመራው ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ትናንት አዲስ አበባ ገብቷል፡፡ ልዑካን ቡድኑ አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲድርስም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ በኪነጥበብ ሰዎች፣ በሀገር ሽማግሌዎች እና አትሌቶች ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል፡፡ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ከስድስት ቀናት በፊት ከኢትዮጵያ ጋር ገንቢ ውይይት ለመጀመር ኤርትራ ልዑካን ቡድኗን እንደምትልክ መናገራቸው ይታወሳል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከኤርትራውያን ልዑካን ጋር ባደረጉት ውይይት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው አለመግባባት እንዲያበቃና ሰላም እንዲፈጠር ጥሪ አቅርበዋል፡፡ «በኢትዮጵያ በኩል ከኤርትራ ጋር የነበረን ለዓመታት የቆየ አለመግባባት እንዲወገድ ከልብ እንፈልጋለን፤ በእኛ በኩል ያለውን ሃላፊነት እንወጣለን» ነው ያሉት፡፡ ምንጭ፡- ሱዳን ትሪቢዩን
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም