በኢትዮጵያ በኮሌራ ወረርሽኝ የ76 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተገለጸ

109
የካቲት 4/2012 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ በተከሰተው የኮሌራ በሽታ ወረርሽኝ እስካሁን የ76 ሰዎች ሕይወት ማለፉን የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ። በሽታው በአሁኑ ወቅትም በኦሮሚያ፣ በደቡብ እና በሱማሌ ክልሎች በወረርሽኝ መልክ እየተሰራጨ ነው ብሏል። ይህ በሽታ "ቫይብሮ ኮሌራ" በተባለ ተህዋስ አማካኝነት የሚከሰትና አንጀትን የሚያጠቃ ነው። ኮሌራ በተህዋሱ በተበከለ ምግብና ውሃ አማካኝነት የሚመጣ ሲሆን አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት ምልክቶቹ እንደሆኑ የሕክምና ባለሙያዎች ያስረዳሉ። የሰውነትን ፈሳሽ በመጨረስ አቅም እንደሚያሳጣና ሕክምና ካላገኘ ምልክት ማሳየት በጀመረ በአምስት ቀናት ውስጥ ለሞት ሊዳርግ እንደሚችልም ይናገራሉ። የኮሌራ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ አብዛኞቹ አካባቢዎች እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ከሚያዚያ 2019 ጀምሮ መከሰቱ ይታወቃል። ወረርሽኙ ተከስቶባቸው ከነበሩ አካባቢዎች መካከል አዲስ አበባን ጨምሮ አማራ፣ ትግራይ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ፣ ድሬዳዋ፣ ሐረር እና ሱማሌ ክልሎች ይጠቀሳሉ። የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በባክቴሪያ የሚመጡ በሽታዎች ቅኝትና ምላሽ ሰጪ ቡድን አስተባባሪ አቶ ሙከሚል ሁሴን ለኢዜአ እንዳሉት በነዚህ አካባቢዎች ወረርሽኙ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ በተሰራው ሥራ በአብዛኞቹ ቦታዎች በሽታውን መቆጠጣር ተችሏል። ይሁንና በኦሮሚያ፣ ደቡብ እና ሱማሌ ክልሎች አሁንም በሽታው በወረርሽኝ መልክ ተሰራጭቶ እንደሚገኝና በበሽታው የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርም እየጨመረ መሆኑን ተናግረዋል። አቶ ሙከሚል እንዳሉት በአጠቃላይ ወረርሽኙ በአገሪቷ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ ሰለባ በሆኑ አካባቢዎች እስካሁን ድረስ ከ4 ሺህ በላይ ሰዎች በበሽታው ተይዘዋል። ካለፈው ዓመት ጀምሮ በተከሰተው በዚሁ የኮሌራ ወረርሽኝ እስካሁን ድረስም 76 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል ነው ያሉት። ወረርሽኙ በአሁኑ ወቅት በደቡብ ክልል በ11፣ በኦሮሚያ በሦስት፣ እንዲሁም በሶማሌ ክልል በሁለት ወረዳዎች በድምሩ በ16 ወረዳዎች እንደሚገኝ ጠቁመዋል። በኦሮሚያ ክልል ወረርሽኙ ዳግም ካንሰራራባቸው አካባቢዎች መካከል ጉጂ ዞን አዶላ ሬዴ እና አባያ ወረዳዎች ይጠቀሳሉ። እንደ አቶ ሙከሚል ገለጻ በደቡብ ክልል በጎፋ ዞን ደብረፀሐይ እና ዛላ ወረዳዎች፣ በጋሞ ዞን ጋራ መርታ ወረዳ እና ከምባ ወረዳ፣ በደቡብ ኦሞ ዞን ሰለማጎ፣ ማሌ እና አሌ ልዩ ወረዳ እንዲሁም በኮንሶ ዞን እና ጌዴኦ ዞን ወናጎ ወረዳ ላይ በሽታው ተከስቷል። በሱማሌ ክልልም እንዲሁ ዳዋ ዞን ሞያሌ ወረዳ ላይ ወረርሽኙ ዳግም መከሰቱን ነው አስተባባሪው የገለጹት። በሽታው በአጭር ጊዜ ለሞት የሚዳርግ በመሆኑ ሕብረተሰቡ ምልክቶቹን በሚያይበት ጊዜ በአፋጣኝ ወደ ሕክምና ተቋም መሄድ እንዳለበትም አሳስበዋል። የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በየዓመቱ ከ1 ነጥብ 3 እስከ 4 ሚሊዮን ሰዎች በኮሌራ በሽታ የሚያዙ ሲሆን ከነዚህ መካከልም ከ21 ሺህ 143 በላይ የሚሆኑት የሰዎች ሕይወት ይጠፋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም