ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ አሁን ያለውን ሰላም ለማጠናከር እየሰራ ነው

70
ዲላ፣ የካቲት 4/2012 (ኢዜአ) የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ሒደቱን ዘላቂና አስተማማኝ ለማድረግ እንዲያግዘው የ100 ቀናት ልዩ ዕቅድ አውጥቶ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ። ዩኒቨርሲቲው ከአካባቢውና ከግቢው ማህበረሰብ ጋር በቅርበት በመስራቱ የመጀመሪያ መንፈቅ ዓመት ትምህርት ካለፉት አመታት አንጻር በተሻለ ሰላምና መረጋጋት አጠናቋል ተብሏል ። የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሰቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጫላ ዋታ ለኢዜአ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት ከአካባቢው ማህበረሰብና ከተማሪዎች ጋር ተቀራርቦ መስራት መቻሉ ለተገኝው አንጻራዊ ሰላምና መረጋጋት ተጠቃሽ ምክንያት ነው ። የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን የጠቀሱት ዶክተር ጫላ በዩኒቨርሲቲው ሁከት ለመፍጠር ሲንቀሳቀሱ በተገኙ 200 ተማሪዎች ፣ መምህራንና የአስተዳደር ስራተኞች ላይ እርምጅ መወሰዱን ተናግረዋል፡፡ ሠላማዊ የመማር ማስተማር ስርዓቱን በማረጋገጥ የልህቀት ጉዞን ማስቀጠል አላማ ያደረገ የ100 ቀናት ልዩ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ትግበራ መገባቱን አስረድተዋል። የዕቅዱ ዋነኛ ትኩረት ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራው ማጠናከር  በመሆኑ ሁሉም ተማሪዎች፣ መምህራንና የአካባቢው ማህበረሰብ በሙሉ ለተግባራዊነቱ እንዲረባረቡ ጥሪ አቅርበዋል ። ካለፉት አመታት አንጻር በመጀመሪያው መንፈቅ አመት የታየው አንጻራዊ ሰላምና መረጋጋት አመቱን ሙሉ እንዲቀጥልም ተማሪዎችን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል ። አስተያየታቸውን ከሰጡ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላት መካከል የ5ኛ አመት የኤሌክትሪካል ምህንድስና ትምህርት ክፍል ተማሪ ዳንኤል እቁባይ እንዳለው የመጀመሪያውን መንፈቅ አመት የመማር ማስተማር ሂደት በሰላም ተጠናቋል። ወደ ዩኒቨርሲቲ የመጣበት ዓላማ መማር በመሆኑ ትምህርቱ ላይ ብቻ በማተኮር ለዩኒቨርሲቲው ዘላቂ ሰላም የበኩሉን እንደሚወጣ ተናግሯል። የመጀመሪያ መንፈቅ አመት ትምህርትን ካለፉት ዓመታት በተሻለ ሰላምና መረጋጋት አጠናቅቆ የመመረቂያ ፕሮጅክት መስራት መጀመሯን የጠቀሰችው ደግሞ የ5ኛ ዓመት የሲቪል ምህድስና ትምህርት ክፍል ተማሪ ዲቦራ መስፍን ናት። ተማሪዎች የሰሙትን ሳያጣሩ ከመቀበል ተቆጥበው ለዩኒቨርሲቲው ሰላምና መረጋጋት የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸውም ምክሯን ለግሳለች ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም