በጋምቤላ ክልል የእንስሳት ጤና አገልገሎትና እርባታን ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ ነው

111
የካቲት 4/2012 (ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል የእንስሳት ጤና አገልገሎትና አርባታ በማሻሻል አርሶና አርብቶ አደሩ ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማስቻል ጥረት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ እንስሳትና ዓሳ ሀብት ቢሮ ገለጸ። በክልሉ 900 ሺህ በላይ የዳልጋ ከብቶች፣ በግና ፍየሎች በሁለት ዙር የተለያዩ በሽታዎች መከላከያ ክትባት በዘመቻ ተሰጥቷል። በቢሮው የእንስሳት ጤና አጠባበቅ ዳይሬክተር ዶክተር አካሉ ከበደ ለኢዜአ እንዳሉት በክልሉ ሰፈ የእንስሳት ሀብት ቢኖረም እስከ ቅርብ ጊዜ ሀብቱን በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል የተከናወነው ስራ ውስን ነው። ቢሮው እራሱን ችሎ ከተደራጀ ሁለት ዓመት ወዲህ የእንስሳት እርባታውንና የጤና አገልግሎት በማሻሻል አርሶና አርብቶ አደሩ ከዘርፉ በተሻለ ተጠቃሚ እንዲሁን ለማስቻል ጥረት እየተደረገ ነው። በተለይም ካለፈው ዓመት ጀምሮ በክልሉ ሁሉም ቀበሌዎች የእንስሳት ጤና ኤክስቴንሽ ባለሙያዎችን በመመደብ የእንስሳት ጤና አገልግሎቱንና የእርባታውን ዘዴ ለማዘመን እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። ዘንደሮም ከዚህ በፊት ባልተለመደ መልኩ በሁለት ዙር ለ930 ሺህ የዳልጋ ከብቶች፣ በግና ፍየሎች የሳንባ ምች፣ የጉረርሳና ደስታ መሰል በሽታዎች መከላከያ ክትባት መሰጠቱን ጠቅሰዋል። በቅርቡም ሶስተኛ ዙር የዳልጋ ከብቶች የጉሮሮ በሽታ መከላከያ ክትባት ለመስጠት አስፈላጊ ዝግጀት መጠናቀቁን ዶክተር አካሉ ገልጸዋል። በላሬ ወረዳ የንብንብ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ዊሊያም አንዲሪው በሰጡት አስተያየት "ካለፈው ዓመት ጀምሮ ለከብቶቻቸው የሚሰጠው የጤናና ሌሎች ሙያዊ ድጋፎች ከቀድሞ  የተሻለ ነው" ብለዋል። በተለይም ዘንድሮ ለከብቶቻቸው በሁለት ዙር ክትባት በመሰጠቱ መደሰታቸውን ተናግረዋል። የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ፖል ጋልዋክ  በበኩላቸው ዘንድሮ ከጣለው ከባድ ዝናብ ጋር ተያይዞ ከብቶቻው ለበሽታ የመጋለጥ ስጋት የነበራቸው ቢሆንም ነገር ግን የክትባት ችግር እንዳላጋጠመቸው ገልጸዋል። በዚህም የከብቶቻቸው ጤንነት በመጠበቁ የተሻለ የወተት ምርት ማግኘታቸውን ጠቁመዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም