ከወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ቲቺንግ ሪፈራል ሆስፒታል ተገቢውን አገልግሎት እያገኘን አይደለም ... ተገልጋዮች

76
ሶዶ ሰኔ 20/2010 ከወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ቲቺንግ ሪፈራል ሆስፒታል ተገቢውን አገልግሎት እያገኙ አለመሆናቸውን ተገልጋዮች ገለጹ። ሆስፒታሉ በበኩሉ በጥናት ላይ የተመሰረተ የመዋቅር ለውጥ የማድረግና ግብአቶችን ለማሟላት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አመልክቷል። አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት ተገልጋዮቹ እንዳሉት የመድኃኒት እጥረት፣ ፈጣን አገልግሎት አለማግኘት እንዲሁም ተገቢ የሕክምና አገልግሎት እጦት ከጠቀሷቸው ችግሮች መካከል ይገኙበታል። በሆስፒታሉ ለመታከም አልጋ ከያዙ አምስት ቀን እንዳለፋቸው የገለጹት ወይዘሮ አብነት ከበደ የተባሉ ተገልጋይ በተላለዩ ጊዜያት ወደሆፒታሉ በመምጣት መታከማቸውን ተናግረዋል። በመስተንግዶ በኩል መጠነኛ መሻሻሎች እንዳለ ቢያስተውሉም ተመርምረው የታዘዘላቸውን መድኃኒት በሆስፒታሉ ማግኘት ባለመቻላቸው ከግል መድኃኒት ቤት ለመግዛት መገደዳቸውንና ይህም ከአቅማቸው በላይ ሆኖ ተስፋ እንዳስቆረጣቸው ገልጸዋል። " ሆስፒታሉ ሪፈራል እንደመሆኑ መጠን የተገልጋዩን ችግር መፍታት በሚያስችል መልኩ አገልግሎቱን መስጠት ይኖርበታል" ሲሉም ተናግረዋል። ጓደኛቸውን ለማስታመም ወደሆስፒታሉ የመጡት አቶ ቢንያም ዳዊት በሆስፒታሉ ሦስት ቀናትን ቢያስቆጥሩም ተገቢውን አገልግሎት ማግኘት እንዳልቻሉ ጠቁመዋል። ችግራቸውን ለሆስፒታሉ ሜድካል ዳይሬክተር ለማሳወቅ ቢፈልጉም "ስብሰባ ላይ ናቸው" በሚል ምክንያት ማግኘት እንዳልቻሉ የገለጹት አቶ ቢኒያም፣ "ከእኔ በተጨማሪ በርካታ ሰዎች በሆስፒታሉ ሰሚ አጥተው እየተንገላቱ ናቸው" ብለዋል። በሆስፒታሉ የተለያዩ አገልግሎት መስጫ ክፍሎች ቢኖሩም ባለሙያ ባለመኖሩ አገልግሎት እንደማይሰጡ ገልጸው፤ በእዚህ ምክንያት ተገልጋዩ እየተጉላላ  በመሆኑ ሆስፒታሉ የጤና ባለሙያዎችን ክፍተት ፈጥኖ እንዲሞላ ጠይቀዋል። የሆስፒታሉ ቺፍ ክሊኒካል ዳይሬክተር ዶክተር ሉቃስ ዲንጋቶ በበኩላቸው ከፍተኛና ጠንከር ያለ ምርመራ ካላስፈለገ በስተቀር ወደ ሆስፒታሉ የሚመጣ ማንኛውም ሕመምተኛ ከአንድ ቀን በላይ እንደማይቆይ ገልጸዋል። የማህበረሰቡን የጤና አገልግሎት እርካታ ለማረጋገጥ እንዲቻል የጥቆማና ቅሬታ ሰሚ ቢሮ በአዲስ መልክ ተዋቅሮ ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል። የተገልጋይ ማህበረሰብ እርካታን ለማረጋገጥ በሦስት ወር ይደረግ የነበረውን የዳሰሳ ጥናት ወደ አንድ ወር ዝቅ እንዲል መደረጉንና የእርካታ መስፈርቶችን በማስቀመጥ በጥናት ላይ የተመሰረተ ምላሽ ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል። የመድኃኒት እጥረትን አስመልክቶ የመንግስት የግዢ ስርዓት የፈጠረው ችግር መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ችግሩን ለመቅረፍ የተለያዩ አማራጮችን ለመጠቀም እየጣሩ መሆናቸውን ተናግረዋል። ሆስፒታሉ ባለበት የላቦራቶሪ ማሽኖች እጥረት ተገልጋዮች ለተጨማሪ ወጪ እየተዳረጉ መሆኑን አምነው በአሁኑ ወቅት የግብአት እጥረቱን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመፍታት ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል። የሆስፒታሉ ቺፍ ኤክሴክዩቲቭ ዳይሬክተር ተወካይ አቶ መለሰ ማላቆ በበኩላቸው እየጨመረ በመጣው የታካሚ ፍሰትና የባለሙያ ቁጥር አለመመጣጠን ምክንያት ተገልጋዮች ለእንግልት እየተዳረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል። ችግሩን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመፍታት በአዲስ የመዋቅር ለውጥ ባለሙያዎችን የማሟላት ሥራ እተከናወነ መሆኑንም አመልክተዋል። " ሆስፒታሉ አሁን ባለበት ደረጃ የተገልጋይን ፍላጎት ማሟላት የሚችልበት አቅም የለውም " ያለት አቶ መለሰ፣ በቀጣይ በቴክኖሎጂ የታገዘና የሪፈራል ሆስፒታል ደረጃውን ያሟላ ሆስፒታል እንዲሆን ለማድረግ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል። የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ቲቺንግ ሪፌራል ሆስፒታል በቀን ከ500 በላይ ሕሙማንን የሚያስተናግድ ሲሆን በወላይታና አካባቢ ዞኖች ለሚገኙ ከ 4 እስከ 5 ሚሊዮን ለሚጠጉ የሕብረተሰብ ከፍሎች አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆኑ ከሆስፒታሉ የተገኘው መረጃ ያሳያል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም