በኢትዮጵያ የአደንዛዥ እፅ ፖሊሲ ትግበራ ቁርጠኝነት ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት እየተካሄደ ነው

142
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 4/2012 ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ አደንዛዥ እፅ ፖሊሲ ትግበራ ባላት ቁርጠኝነት ላይ ትኩረቱን ያደረገ አውደ ጥናት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው። በአውደ ጥናቱ ላይ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሊያ ታደሰ፣ የመንግስታቱ ድርጅትና የአፍሪካ ሕብረት ተወካዮችን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል። አውደ ጥናቱ በአደንዛዥ እፅ ዙሪያ ያለውን የግንዛቤ እጥረት ለማቃለልና በአገር ፣ በአህጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ችግሩን ለመፍታት ያለመ መሆኑ ተነግሯል። በተጨማሪም ዓለም አቀፋን የአደንዛዥ እፅ ፖሊሲ ለመተግበር አገራት ያላቸው ቁርጠኝነት ላይ ያተኮረም ነው ተብሏል። በአውደ ጥናቱ ላይ እንደተመለከተው በቀጣዮቹ 30 ዓመታት ከሠሃራ በታች ያሉ አገራት ከዓለም ትልቁን አደንዛዥ እፅ ተጠቃሚ አገራት ይሆናሉ ተብሎ ከወዲሁ ተገምቷል። ምስራቅ አፍሪካም ከፍተኛውን አደንዛዥ እፅ በመጠቀም የአደንዛዥ እፅ ገበያውን እንደምትመራም እንዲሁ። ይህን አስጊ ሁኔታ ለማስቆም አገራት የሚኖራቸው ቁርጠኝነት ወሳኝነት እንዳለው ተገልጿል። በአውደ ጥናቱ ላይ ከፌዴራል፣ ከክልል፣ ከአፍሪካ፣ ከዓለም አቀፍ፣ ከሲቪል ማህበረሰብና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት መሳተፋቸው ታውቋል። ዛሬ የተጀመረው አውደ ጥናት አስከ መጪው ዓርብ እንደሚካሄድ ከወጣው መርሀግብር ለማወቅ ተችሏል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም