የአፍሪካ ወጣቶች መንግስታት የሚያስተላልፏቸውን ውሳኔዎች በተግባር እንዲያሳዩ ጠየቁ

77

አዲስ አበባ፤ የካቲት 4/2012 የአፍሪካ ወጣቶች መንግስታት በስራ ዕድል ፈጠራ ላይ የሚያስተላልፏቸውን ውሳኔዎች በተጨባጭ እንዲያሳዩ ጠየቁ።

የአፍሪካ ግብርና ምርምር ፎረም በበኩሉ የግብርናው ዘርፍ በርካታ የስራ ዕድል መፍጠር የሚያስችል በመሆኑ መሪዎች ትኩረት እንዲሰጡት ጠቁሟል።

በ33ኛው የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ የታደሙ የተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ወጣቶች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት መሪዎቻቸው በጉባዔ የሚያስተላልፏቸውን ውሳኔዎች ተግባር ላይ እንዲያውሉ ጠይቀዋል።

አፍሪካዊያኑ መሪዎች በየዓመቱ በሚያካሂዱት ጉባዔ በበርካታ አጀንዳዎች ላይ በመወያየት ውሳኔ እንደሚያሳልፉ አስታውሰዋል ወጣቶቹ።

የወጣቶች ስራ ዕድል ፈጠራ፣ ጤና፣ ንግድ፣ መሰረተ ልማት፣ አህጉራዊ ትስስርና የምጣኔ ሃብት ዕድገትን ከአጀንዳዎቹ መካከል ጠቅሰዋል።

እናም ከአህጉሪቷ ሕዝብ ከ60 በመቶ በላይ በሚሆነው ወጣት ላይ የሚተላለፉ ውሳኔዎችን በተግባር ማየት እንደሚፈልጉ ነው በአጽንኦት የተናገሩት።

መሪዎቹ የሚያስተላልፏቸውን ውሳኔዎች የጊዜ ሰሌዳ በማውጣት የወጣቶችን የምጣኔ ሃብት ተሳትፎና ተጠቃሚነት በተግባር እንዲያረጋግጡ ጠይቀዋል።

ቀጣዩ ጉባዔያቸው የተገኙ ለውጦችን እንዲሁም የተጀመሩ ስራዎች ያሉበትን ደረጃ የሚያቀርቡበት ሊሆን እንደሚገባም ተናግረዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል ኬንያዊው ወጣት ሮናልድ ሙትዬ  ቀጣዩ ስብሰባ ስኬቶችና ሂደቶችን የምንሰማበት እንጂ  ሁልጊዜ ችግሮችን ብቻ የምንሰማበት መሆን የለበትም ብሏል፡፡

ኢትዮጵያዊቷ ወጣት ሊዲያ ምትኩ በበኩሏ"ለወጣቱ ራዕይ መስጠት፣ ተስፋ መስጠት፤ የሚሰማራባቸውን ስራዎች በመፍጠርና በማደራጀት ወደ አላስፈላጊ ነገር እንዳይገቡ ማድረግ ይገባል" ነው ያለችው፡፡

በትምህርት ላይ ብዙ መዋዕለ ነዋይ በማፍሰስ  ወጣቶች ራሳቸውን በማብቃት ስራ ፈጣሪዎች ይሆናሉ፣ ወደ ጦርነት ከመሄድ ይልቅ የሚለን የጋምቢያው ወጣት ፋቱ አህመድ ነው፡፡

በአፍሪካ ግብርና ምርምር ፎረም ከፍተኛ ተመራማሪ አንሰልሚ ቮዱንሂሲ በበኩላቸው የአፍሪካ መሪዎች ስለ ወጣቶች ስራ ዕድል ፈጠራ የግብርናውን ዘርፍ ዕድል መጠቀም እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

አፍሪካ በዓመት ምግብ ከውጭ ለማስገባት በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር እንደምታወጣ ገልጸው ወጣቱን በዚህ ዘርፍ በማሰማራት ወጪውን ማዳን እንደሚቻል ይመክራሉ።

አብዛኛው ሕዝቧ በግብርና በሚተዳደርባት አፍሪካ ምርቶች ላይ እሴት በመጨመር በኩል ብዙም እንዳልተሰራም ያነሳሉ።

በዚህም ምክንያት በቀላሉ ሊመረቱ የሚችሉ የተቀነባበሩ የግብርና ምርቶች ከሌሎች አገራት እየገቡ መሆኑን በቁጭት አንስተዋል።

የግብርና ማቀነባበሪያዎችን በማልማትና እሴት በመጨመር ወጣቶች መሳተፍ የሚችሉበት ዕድል ሰፊ መሆኑንም ገልጸዋል።

የአፍሪካ ግብርና ባለመዘመኑ ምክንያት ስራውን እያከናወኑ የሚገኙት በዕድሜ የገፉ ሰዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም ግብርናውን በዘመናዊ አሰራር በማገዝ ወጣቶችን ማሰማራት እንደሚቻል አንስተዋል።

እንደ ተመራማሪው ገለጻ መሪዎች ወጣቶችን ጨምሮ በአህጉሪቷ ጉዳይ የሚያስተላልፏቸውን ውሳኔዎች በተግባር የሚያሳዩባቸውን አማራጮች እንዲያዩ መክረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም