የጥይት ድምጽ የማይሰማባት አፍሪካን ለመፍጠር ወጣቶች በመንግስታት ላይ ጫና ሊያደርጉ ይገባል

75
አዲስ አበባ ( ኢዜአ) የካቲት 3/2012 የጥይት ድምጽ የማይሰማባት አፍሪካን የመፍጠር ዘመቻው እውን እንዲሆን ወጣቶች በመንግስታት ላይ ጫና እንዲያደርጉ በአፍሪካ ሕብረት የወጣቶች ልዩ መልዕክተኛ አያ ቺቢ ጠየቀች። ልዩ መልዕክተኛዋ 33ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ትናንት ሲጠናቀቅ ለኢዜአ እንደገለጸችው የበርካታ ወጣቶችን ሕይወት እየቀጠፈ ያለው ጦርነት ሊያበቃ ይገባል። "የጥይት ድምጽ የማይሰማባት አፍሪካን ለመፍጠር እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ እውን ለማድረግ የተቀናጀ ጥረት ያስፈልጋል" ትላለች። እ.አ.አ በ2063 አፍሪካ የበለጸገችና ሠላም የሰፈነባት፤ ወጣቶችና ሴቶች በምጣኔ ሃብት፣ በአመራር ሰጪነት እንዲሁም በፖሊሲ አውጪነት በመሳተፍ ተጠቃሚ የሚሆኑባት አህጉር እንድትሆን ከወዲሁ መስራት ያስፈልጋል። እንደ ልዩ መልዕክተኛዋ ገለጻ ይህን እውን ለማድረግ ሴቶችና ወጣቶች ትልቅ ሚና አላቸው። በመሆኑም አጀንዳዎችን በመቅረጽ፣ ወደ ጦርነት ከሚወስዱ ድርጊቶች በመቆጠብ፣ የወጡ ፖሊሲዎች እንዲተገበሩ ሠላማዊና ሌሎች መንገዶችን በመጠቀም በመንግስታት ላይ ጫና እንዲደረግ ጠይቃለች። በአህጉሪቱ የወጣቶች መገለጫ የሆነውን ስራ አጥነት፣ ስደት፣ አመጽና ሌሎች የተሳሳቱ ትርክቶችን መቀየር እንደሚያስፈልግም ገልጻለች። አፍሪካ የምትፈልገውን ለውጥ ለማምጣት ያላትን ወጣት ኃይል ለፈጠራና ለሠላም ማስፈን መጠቀም ጊዜው አሁን እንደሆነም ነው የተናገረችው። የጥይት ድምጽ የማይሰማባት አፍሪካን የመፍጠር እንቅስቃሴን እውን ለማድረግ ዘመቻ መጀመሩን ጠቁማ ወጣቶች ይህንን እንዲቀላቀሉም ጥሪ አቅርባለች። ልዩ መልዕክተኛዋ መንግስታት ወጣቶችን በውሳኔ ሰጪነት፣ በፖሊሲ፣ በምክር ቤት፣ በሲቪል ማህበርና ሌሎች ዘርፎች በማካተት ስር ነቀል ማምጣት እንደሚቻል ያላትን እምነትም ገልጻለች። የአፍሪካ መሪዎች አፍሪካን በሚመለከቱ ውሳኔዎች ላይ ወጣቶችን እንዲያሳትፉ በመጠየቅ። ትናንት የተጠናቀቀው 33ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ስብሰባ ትኩረቱን "የጥይት ድምጽን በማስቆም ለምጣኔ ሃብት እድገት የተመቸች አፍሪካን እንፍጠር" በሚል መሪ ሀሳብ ነው የተካሄደው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም