ዓመታዊው የመከላከያ ሠራዊት ቀን የካቲት 7 ይከበራል

184

አዲስ አበባ የካቲት 03 / 2012 ( ኢዜአ ) የመከላከያ ሠራዊት ቀን የካቲት 7 ቀን 2012 ዓ.ም ይከበራል።

የዘንድሮው የመከላከያ ሠራዊት ቀን "የሀገራችንን ሉዓላዊነትና የሕዝባችንን ሠላም በፅናት እንጠብቃለን" በሚል መሪ ሃሳብ እንደሚከበር ታውቋል።

ሚኒስቴሩ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው በዓሉ ከሕብረተሰቡ ጋር በሚደረጉ ውይይቶች፣ በበጎ አድራጎት ስራዎች፣ በስፖርታዊ ውድድሮች፣ የሠራዊቱን ዝግጁነት በሚያሳዩ ወታደራዊ ሰልፎችና ትርዒቶች ታስቦ ይውላል።

ቀኑ እስካሁን ሠራዊቱ የሔደባቸው ጉዞዎች የሚቃኙበት፣ ሕዝባዊ ወገንተኝነቱን በማረጋገጥም እንዳለፉት ጊዜያት ሁሉ ተልዕኮውን በጽናት ለመወጣት ያለውን ዝግጁነት የሚያሳይበት ነው ብሏል።

ሠራዊቱ የሕዝቡን ሠላም በጽናት ለመጠበቅ በቁርጠኝነት እንደሚሰራም ሚኒስቴሩ ገልጿል።

በተጨማሪም የሠራዊቱ አባላት የአገሪቷን ሉዓላዊነትና የሕዝቦችን ሠላም በጽናት ለመጠበቅ ቃላቸውን  የሚያረጋግጡበት መሆኑም ተመልክቷል።

ከሁሉም በላይ የሠራዊቱ አባላት የአገሪቷን ሉዓላዊነትና የሕዝቦችን ሠላም በጽናት ለመጠበቅ ለሕዝቡ ቃል የሚገቡበት መሆኑም በመግለጫው ተጠቅሷል።

"ቀኑ ከሕብረተሰቡ፣ ከፀጥታ ኃይሎችና ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ጠንክሮ በመስራት በታማኝነት፣ በሕዝባዊነትና በፍጹም ገለልተኝነት የአገርን ደህንነትና የሕዝቡን ሠላም ከማንኛውም ጥቃት እንደምንከላከል ዳግም ቃላችንን የምናድስበት ነው" ይላል መግለጫው።

ሠራዊቱ ለሕዝቡና ለአገሩ ያለውን ታማኝነትና ፍቅር በመግለጽ ቃሉን የሚያድስበት ቀን እንዲኖረው በማስፈለጉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በወሰነው መሰረት የካቲት 7 ቀን 'የሠራዊት ቀን' ተብሎ በየዓመቱ ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም