በዋግ ኽምራ ለሚገኙ ጤና ጣቢያዎች የዘጠኝ አምቡላንሶች ድጋፍ ተደረገ

89
ሰቆጣ ፣የካቲት 3/2012  (ኢዜአ) በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን የእናቶችና ህፃነትን ሞት ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት የሚያግዙ ዘጠኝ አምቡላንሶች በድጋፍ ማግኘቱን የዞኑ ጤና መምሪያ ገለፀ ፡፡ የመምሪያው ምክትል ሃላፊ አቶ አሳየ ገብረስላሴ ለኢዜአ እንደገለፁት ተሽከርካሪዎቹ የእናቶች እና ህፃናትን ሞት ለመቀነስ ለሚደረገው እንቅስቃሴ  አይነተኛ ሚና ይጫወታሉ። በተለይም ከዚህ በፊት በአምቡላንስ እጥረት እናቶች በህክምና ተቋማት በሰለጠነ ባለሙያ እንዲወልዱ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት እንቅፋት ፈጥሮ መቆየቱን ጠቅሰዋል። አምቡላንሶቹ ነፍሰጡር እናቶችን በፍጥነት ወደ ጤና ተቋማት እንዲደርሱ በማድረግ የእናቶች እና ህፃናት ሞትን ለመቀነስ ያግዛሉ ብለዋል። እንዲሁም ለ25 ሺህ ህዝብ አንድ አምቡላንስ የሚለውን መርህ በዞኑ ለማሳካት የላቀ ሚና እንዳላቸው አመልክተዋል። በዚህም የተፈራ ሃይሉ ሆስፒታልን ጨምሮ በስምንት ወረዳዎች ለሚገኙ ጤና ጣቢያዎች አምቡላንሶቹ መመደባቸውን ጠቅሰው በሁሉም አምቡላንሶች የድንገተኛ አደጋዎች የህክምና ባለሞያዎች መመደባቸውንም ተናግረዋል። አምቡላንሶቹ ለታለመላቸው ዓላማ ብቻ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል ከወረዳ አስተዳዳሪዎች እና የጤና ጣብያ ሃላፊዎች ጋር የመግባቢያ ሰነዶች ይዘጋጃሉ ያሉት ምክትል ሃላፊው ከታለመላቸው ዓላማ ውጭ አገልግሎት ሲሰጡ ለሚመለከተው አካል መጠቆም የሚችሉ ስልክ ቁጥሮችም  በተሽከርካሪዎች በር ላይ በግልፅ እንደሚፃፍ አስረድተዋል ። ከጤና ሚኒስቴር የተለገሱት አምቡላንሶች በብሄረሰብ አስተዳደሩ ያሉትን የአምቡላንስ ቁጥር ወደ 29 ከፍ እንዳደረገው ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል ። በዝቋላ ወረዳ የሚገኘው የተላጀ ጤና ጣብያ ሃላፊ አቶ አለባቸው ጌታወይ በበኩላቸው ጤና ጣቢያው የራሱ የሆነ አምቡላንስ ባለመኖሩ ህሙማንን ለማስተናገድ ችግር ሲገጥመው መቆየቱን አስታውሰዋል። በተለይም ለከፍተኛ ህክምና ወደ ሰቆጣ ሆስፒታል ሪፈር ለሚላኩ ህሙማን አምቡላንስ ተደውሎ እስኪመጣ ቢያንስ እስከ ሁለት ሰአት ድረስ ለመጠበቅ ይገደዱ እንደነበር ገልፀዋል። በዚህም እናቶች በወሊድ ወቅት ለከፍተኛ ስቃይ ይጋለጡ እንደነበር ጠቅሰው አሁን ላይ ለጤና ጣቢያው አምቡላንስ መመደቡ ችግሩ ይቀርፈዋል የሚል ተስፋ አሳድሯል ። የአምቡላንሱ መመደብም በእናቶችና ህፃናት እነዲሁም በሌሎች ሰዎች ላይ የሚከሰትን ድንገተኛ የጤና እከል አጓጉዞ ህክምና ለመስጠት እንደሚያስችል አቶ አለባቸ ተናግረዋል ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም