በመቀሌ ከተማ የትራፊክ መቆጣጠሪያ መብራቶች ተከላ እየተካሔደ ነው

75
መቀሌ፣ የካቲት 3 / 2012 (ኢዜአ) በመቀሌ ከተማ በ60 ሚሊዮን ብር ወጪ ነባር የትራፊክ መብራቶች የመጠገንና አዳዲስ መብራቶችን የመትከል ስራ እየተካሔደ መሆኑን የከተማው የተቀናጀ የመሰረተ ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ። የፅህፈትቤቱ ኃላፊ አቶ ሃፍቱ መብራህቱ ለኢዜአ እንደገለፁት በመቀሌ ከተማ የተሽከርካሪዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። ''የተሽከርካሪዎቹ እንቅስቃሴ ለመቆጣጠርና ያለውን የትራፊክ መጨናነቅ ለመፍታት የመቆጣጠሪያ መብራቶችን በዋና ዋና የጉዞ መስመሮች ላይ መትከል አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል'' ያሉት ኃላፊው 60 ሚሊዮን ብር በጀት ተመድቦ ወደ ስራ መገባቱን ገልፀዋል። በጀቱ የተመደበው የተበላሹ ሰባት ነባር የትራፊክ መብራቶች ለመጠገንና በ18 የጉዞ መስመሮች ላይ አዳዲስ መብራቶች ለመትከል መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል። ቀደም ሲል የትራፊክ መቆጣጠሪያ መብራቶቹ ብልሽት ሲያጋጥማቸው ጠጋኞች ከአዲስ አበባ ስለሚጠሩ የመዘግየት ችግር ሲገጥማቸው እንደነበር አስታውሰዋል። ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ በዘርፉ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን የማዘጋጀት ስራ ጎን ለጎን ሲካሔድ መቆየቱንም አቶ ሃፍቱ ገልፀዋል። ነባሮችን የመጠገንና አዳዲስ የትራፊክ መቆጣጠሪያ መብራቶችን የመትከል ስራ በዘንድሮው የበጀት ዓመት ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃል ተብሏል። በመቀሌ ከተማ የሀውልት ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ በርሃኑ ሃይላይ በሰጡት አስተያየት ነባር የትራፊክ መቆጣጠሪያ መብራቶች ሲበላሹ በፍጥነት ስለማይጠገኑ በተሽከርካሪዎች ፍሰት ላይ መስተጓጎል ያጋጥም ነበር። አሁን ጥገናና አዳዲስ የትራፊክ መቆጣጠሪያ መብራቶች ተከላ መከናወን መጀመሩ መልካም ቢሆንም ብልሽት ሲያጋጥም ፈጥኖ የመጠገን ስራ ትኩረት እንዲሰጠው ጠቁመዋል። በከተማው ተተክለው ከነበሩ በርካታ የትራፊክ መቆጣጠሪያ መብራቶች መካከል አገልግሎት የሚሰጠው አንድ ብቻ ነው ያሉት ደግሞ የሓድነት ክፍለ ከተማ ነዋሪ መምህር ርሻን ገብረክርስቶስ ናቸው። ብዙ ገንዘብና እውቀት ወጥቶባቸው ሲበላሹ በወቅቱ ካልተጠገኑ የሃብት ብክነት የሚያስከትል በመሆኑ የሚመለከተው አካል ትኩረት እንዲሰጥበት አሳስበዋል። የከተማ አውቶቡስ ሾፌር አቶ ስዩም ኪዳነማርያም በበኩላቸው የትራፊክ መጨናነቅ በሚበዛባቸው መስመሮች የተተከሉ የትራፊክ ምልክቶች አደጋን ከመቀነስ አንፃር ጠቀሜታቸው የጎላ በመሆኑ አንክብካቤ ያስፈልጋቸዋል። በትግራይ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የትራፊክ ደህንነት ፖሊስ ፅህፈት ቤት አስተባበሪ ኮማንደር ብርሃነ መስቀል በየነ እንደገለፁት የመብራቶቹ አገልግሎት ማቆም በስራቸው ላይ ጫና እየፈጠረባቸው መቆየቱን በማስታወስ በከተማው የተቀናጀ ልማት ጽህፈት ቤት በኩል የተጀመረው ጥረት የሚያስመሰግን ነው ብለዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም