የአፍሪካ ኀብረት የ10 ዓመት የመሰረተ ልማት ዕቅድ ተጠናቀቀ

100

አዲስ አበባ፤ የካቲት 2/2012 የአፍሪካ ኀብረት የአህጉሩን ኢኮኖሚ ለማስተሳሰር የያዘውን አጀንዳ የሚያስፈጽም የ10 ዓመት የመሰረተ ልማት ዕቅድ ማጠናቀቁን አስታወቀ።

በኀብረቱ የመሰረተ ልማትና ኢነርጂ ኮሚሽነር ዶክተር አቡ-ዚድ አማኒ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ የኀብረቱ የልማት አጀንዳ በሆኑት በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ፣ በትራንስፖርት፣ በኢነርጂና በቱሪዝም ዘርፎች የ10 ዓመት ዕቅድ ተጠናቋል።

የልማት ዕቅዱ በስራ ዕድል ፈጠራና በመሰረተ ልማት ግንባታዎች ዜጎችን ከድህነት ማውጣት ትኩረት ያደረገባቸው ነጥቦች እንደሆኑም ኮሚሽነሯ አብራርተዋል።

እንደ ዶክተር አቡ-ዚድ አማኒ ማብራሪያ የአፍሪካ ኀብረት በያዘው የልማት አጀንዳ መሰረት አህጉሪቱን በመሰረተ ልማት በማስተሳሰር ተወዳዳሪ የሆነ ኢኮኖሚን የመገንባት ዓላማ አለው።

ኮሚሽኑ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2012 እስከ 2020 ድረስ ያለውን የአፍሪካ የመሰረተ ልማት መርሐ ግብር አጋማሽ ግምገማ ያጠናቀቀ ሲሆን በግምገማውም በአፈጻጸም ረገድ የተገኙ ቁልፍ ግኝቶችና ውጤቶች መለየታቸውን ተናግረዋል። ከ2021 እስከ 2030 ድረስ ተግባራዊ የሚደረገው ሁለተኛው ምዕራፍ የአፍሪካ የመሰረተ ልማት ፕሮግራም ቅድሚያ የተሰጣቸው ተግባራት በሚቀጥለው ዓመት በሚካሄደው የኀብረቱ ጉባዔ ይፋ እንደሚደረጉም አመልክተዋል። በሁለተኛው ምዕራፍ ተግባራዊ በሚደረገው የልማት መርሐ ግብር ስርዓተ ፆታን ያካተተ የእሴት ሰንሰለት ያለው የ135 ቢሊዮን ዶላር ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀት እንደሚጠበቅም ኮሚሽነሯ ጠቁመዋል። የልማት መርሐ ግብሩ ጠንካራ ማዕቀፍ ያለው ሲሆን ቅድሚያ የተሰጣቸው አገራዊና ድንበር ተሻጋሪ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች በመላው አህጉሪቱ ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑን አብራርተዋል። "የትራንስፖርት ዘርፉም የአፍሪካ አህጉርን የሚያገናኝ፣ ተለዋዋጭና ድንበሮችን የሚያስተሳስር የአፍሪካ የተቀናጀ ባለከፍተኛ ፍጥነት የባቡር መስመር ኔትዎርክ ፕሮጀክት እንዲሁም አንድ የአየር ትራንስፖርት ገበያ እንዲኖረው ይደረጋል’’ ብለዋል። ኮሚሽኑ በአፍሪካ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ እንዲሁም ለዲጂታል አፍሪካ ፖሊሲ እና ደንብ ተነሳሽነት በሚሉ ሁለት አንኳር ጉዳች ላይ እየሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል። በኢነርጂ ዘርፍ ደግሞ የአፍሪካ ኀብረት ኮሚሽን አህጉራዊ የኤሌክትሪክ ገበያ፣ የኃይል ማከፋፈያ መሪ ዕቅድ፣ የጂኦተርማል ስጋትን ለመላመድ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር የአፍሪካ የኢነርጂ መረጃ ስርዓትና የኢነርጂ ትራንስፎርሜሽን መርሐ ግብር የተያዙ ዕቅዶች ናቸው። የአፍሪካ የኢነርጂ መረጃ ስርዓት ዓላማ ከፍተኛ መጠን ያለው ትክክለኛ አሀዝ የኢነርጂ መረጃና ዳታ መሰብሰብ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም