ዩኒቨርሲቲው የምርምር ውጤቶች ጥቅም ላይ እንዲውሉ ጥረት እያደረገ ነው

102
ደብረብርሃን፣ የካቲት 2/2012 (ኢዜአ)  የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በየዓመቱ በምሁራን የሚሰሩ የምርምር ውጤቶች ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለማስቻል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገለጸ። በምርምር ስራዎችና ቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ ዛሬ በዩኒቨርሲቲው  ውይይት ተካሄዷል። በውይይቱ ወቅት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ንጉስ ታደሰ  እንዳሉት የተቋሙ  ምሁራን በተለዩ ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎች እያካሄዱ ነው። እውቀትና ከፍተኛ ሃብት ፈሶባቸው የሚከናወኑ የምርምር ስራዎችን ወደ ተግባር የማስገባት ሙከራ ቢኖርም የሚፈለገውን ያህል ውጤታማ እንዳልሆኑ ተናግረዋል። ባለፉት ዓመታት ከ300 በላይ የምርምር ስራዎች ቢከናወኑም እውቅና ተሰጥቷቸው ወደ ተግባር የገቡት በቁጥር አነስተኛ መሆናቸውን አመልክተዋል። በመንዝ በግ፣ በጅሩ ሰንጋ፣ በደብረሲና ቆሎ፣ በምንጃር ጤፍና ሽምብራ ምርምር ውጤቶች ከኢትዮጵያ አእምሮአዊ ንብረት የባለቤትነት ምስክር ወረቀት እንዲያገኙ በመጥቀስ። ሆኖም  አብዛኛዎቹ የምርምር ውጤቶች መደርደሪያ ላይ የቀሩ መሆናቸውን ገልጸው "ከዚህ በኋላ ወደ ተግባር በማስገባት የህብረተሰቡን ተጨባጭ ችግር መፍታት ይገባቸዋል" ብለዋል። ችግሩን ለመፍታትም ከዚህ በፊት የተሰሩ የጥናትና ምርምር ውጤቶችን ወደ ተግባር ለማሸጋገር ኮሚቴ ተቋቁሙ  እየተለዩ  መሆናቸውን ዶክተር ንጉስ አስታውቀዋል። የምርምር ስራዎችም ተመራማሪዎቹን በመደገፍ ፈጥነው ወደ ተግባር ገብተው ጥቅም እንዲሰጡ ጥረት እየተደረገ  ነው። በዩኒቨርሲቲው ሰላማዊ የመማር ማስተማር በዘላቂነት እንዲቀጥል በግጭት መንስኤዎችና መፍትሄዎቻቸው ዙሪያ ቡድን ተደራጅቶ ጥናት በመካሄድ ላይ እንደሆነም አብራርተዋል። በዩኒቨርሲቲው የጥናትና ምርምር ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር አልማዝ አፈራ በበኩላቸው በየጊዜው የሚደረጉ ጥናትና ምርምሮች የህዝቡን ችግር በዘላቂነት የሚፈቱ መሆን አለባቸው ብለዋል። የውይይቱ ዓላማም ያለፉትን የምርምር ውጤቶች አተገባበር በመገምገም ችግሮቹ ላይ ተወያይቶ ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት እንደሆነ ገልጸዋል። "በተለይም የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ፣ ለሰላምና አንድነት እንዲሁም ለምርታማነት ማደግ አስተዋጽኦ ለሚያደርጉ የምርምር ስራዎች ጠንካራ ድጋፍ ይደረጋል" ብለዋል። በዩኒቨርሲቲው የዳበረ አስተሳሰብ ያለው ትውልድ ለማፍራት በጥናት  ታግዞ መሰራት እንዳለበት ያመለከቱት ደግሞ  የውይይቱ ተሳታፊ ዶክተር አስራተ መድህን በቀለ ናቸው። "ዩኒቨርሲቲዉ በምርምር ሆነ ሌሎች የተግባር ስራዎች በየጊዜው እየተገናኙ መመካከሩም ችግሮችን ፈጥኖ ለማስተካከል ያግዛል" ብለዋል። ተሳታፊዎቹ ለምርምር የሚውል የበጀት አጠቃቀም ጉድለት እንዲስተካከልም ጠቁመዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም