የኀብረቱ አባል አገሮች ለሰላም ፈንድ ተጨማሪ 10 ሚሊዮን ዶላር አዋጡ

65
የካቲት 2/2012 (ኢዜአ) የአፍሪካ ኀብረት አባል አገሮች ለሰላም ፈንድ ከሚያዋጡት ዓመታዊ መደበኛ መዋጮ በተጨማሪ 10 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ዛሬ ጠዋት መስጠታቸውን የኀብረቱ የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት ኮሚሽነር አምባሳደር ስማይል ቼርጉይ ገለጹ። የኀብረቱ አባል አገሮች ለሰላም ፈንድ የሚያዋጡት መደበኛ መዋጮ በአህጉሪቱ የሚከሰቱ ግጭቶችን ለመከላከል ለሚከናወኑ ተግባራት የሚውል መሆኑን ተናግረዋል። ‘’ለአባል አገሮቹ ዛሬ ጠዋት በተደረገ ጥሪ በየዓመቱ ከሚያዋጡት መደበኛ መዋጮ ሌላ ለሰላም ፈንድ የሚውል ተጨማሪ 10 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር መዋጮ ቀርቧል’’ ብለዋል። እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ፤ ዛሬ ከቀረበው 10 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ውጭ በኀብረቱ የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት በኩል ከአባል አገሮች የተሰበሰበ ዓመታዊ መደበኛ መዋጮ 144 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር አለ። ‘’የሰላም ፈንዱ በአጉሪቱ በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ዓመጽ እና ግጭቶች ለማስቆም የሚደረገውን ጥረት ያግዛል’’ ብለዋል። ከአባል አገሮቹ የሚገኘው ተጨማሪ መዋጮ የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት በቅርቡ በሙሉ አቅሙ በርካታ ተግባራትን ለማከናወን እንደሚያስችለውም አስረድተዋል። የሰላም ፈንድ ፋይናንስ ለሦስት አበይት ተግባራት የሚውል መሆኑን የጠቆሙት ኮሚሽነሩ በተለይ ለማሸማገልና ለመከላከል ዲፕሎማሲ፣ ለተቋማዊ አቅም ግንባታና በአህጉሪቱ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ የሚውል እንደሆነም ገልጸዋል። በአህጉሪቱ ለሚከናወኑ የሰላም ማስከበርና ሽብርተኝነትን ለመከላከል በሁሉም አገሮች ተቋማዊ አቅምን ለመገንባት አንድ ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም