የተጣለባቸው የግብር ቅጣት ፍትሃዊነት እንደሌለው በነገሌ ከተማ ነጋዴዎች ቅሬታቸውን ገለጸ

81

ነገሌ ኢዜአ የካቲት 2/2012፡- በግብር ሰብሳቢው መስሪያ ቤት የተጣለባቸው ቅጣት ያልተጠራና ፍትሃዊነት የሌለው መሆኑን በጉጂ ዞን ነገሌ ከተማ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነጋዴዎች ቅሬታቸውን ገለጸ።

የጉጂ ዞን ገቢዎች ባለስልጣን ጽህፈት ቤት በበኩሉ ግብር ለመሰወር የሞከሩ 210 ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን አመልክቷል።

ወይዘሮ ሊና መኮንን በነገሌ ከተማ የህንጸ መሳሪያ አቅራቢ ድርጅት ባለቤት ሲሆን ስራና ሰላም ባለ ጊዜ  እስከ 100 ሺህ ብር የተጨማሪ ታክስ እሴት ገንዘብ እየሰበሰቡ ለመንግስት ገቢ ሲያደርጉ እንደነበር አስታውሰዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በጸጥታ ችግር የገበያ ሁኔታ እየተቀዛቀዘ በመምጣቱ ከደንበኞቻቸው የሚሰበስቡት የተጨማሪ ታክስ እሴት ገንዘብ ወደ 10 ሺህ ብር ዝቅ ማለቱን ተናግረዋል፡፡

በዚህ ምክንያት ገበያ ባለመኖሩ እንጂ ግብር ለመሰወር አስበው የተጨማሪ ታክስ እሴት ሳይቆርጡና ደረሰኝ ሳይሰጡ እንዳልሸጡ ያመለከቱት ወይዘሮ ሊና፤  ይህ ሁነታ ሳይጣራ የተጣለባቸው ቅጣት ፍትሃዊ እንዳልሆነ ገልጸዋል።፡

በቀጣይም የንግድ ህግን አክብረው እንደሚሰሩና የመንግስትን ገቢ በአግባቡ የሚሰበስቡ በመሆኑ ግብር ሰብሳቢ መስሪያ ቤት  በመረጃ የተደገፋና ፍትሃዊ አሰራር ሊከተል እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

ሌላው በንግድ ስራ የተሰማሩት  ወይዘሮ ሀለዊያ ቡሃሪም በበኩላቸው ግብር ሰብሳቢው  መስሪያ ቤት  አለአግባብ  ቅጣት በመጣል ህጋዊ ነጋዴውን ማሳደድ ማቆም እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

"በራሳቸው ህጉን ተከትለው እንደሚሰሩና ከህግ ውጭ ቫት ሳይቆርጡ መሸጥ ፍትሃዊ የንግድ ውድድርን ከማዛባት አልፎ የሰላምና የልማት እንቅፋት ነው " ያሉት ደግሞ በከተማው የሀዊ ሆቴል ባለቤት አቶ ግዛቸው ካሳ ናቸው።

አቶ ግዛቸው እንዳሉት ግብር ሰብሳቢው መስሪያ ቤት በህገወጥ ነጋዴች ላይ የጀመረውን ክትትልና ቁጥጥር በማጠናከር ፍትሃዊ የንግድ ውድድር እንዲያሰፍንና ለህጋዊ ነገዴዎች ድጋፍ ማድረግ አለበት፡፡

በመስሪያ ቤቱ አለአግባብ የሚጣልባቸው የግብር ቅጣት  ህጋዊና ህገወጡን መለየት ያልቻለ ፍትሃዊነት የጎደለው መሆኑን አስተያየት ሰጪዎቹ ጠቁመዋል፡፡

የዞኑ ገቢዎች ባለስልጣን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አጋ ጎበና  በበኩላቸው ቅሬታው ተገቢነት እንደሌለው ገልጸው ግብር ለመሰወር የሞከሩ 210 ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን አመልክተዋል።

በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ ከተወሰደው እርምጃ የገንዘብ ቅጣት ይገኝበታል።

የተቀጡትም 3 ሚሊዮን ብር  መሆኑን ኃላፊው ጠቅሰዋል።

በገንዘብ የተቀጡት ለተጠቃሚው  የተጨማሪ ታክስ እሴት ደረሰኝ ሳይሰጡ ሲሰሩ የተገኙና ባጠፉት ጥፋት ያልተጸጸቱ 110 ነጋዴዎች ናቸው።

ፍትሃዊ ያልሆነ ዋጋ በመጨመር እጅ ከፍንጅ የተያዙና ይቅርታ በመጠየቅ ከጥፋታቸው ለመታረም ዝግጁ የሆኑ 100 ነጋዴዎች ደግሞ በጽሁፍ ማስጠንቀቂያ መታለፋቸውን የጽህፈት ቤት ኃላፊ አመላክተዋል።

በዞኑ ባለፈው ዓመት ግብር ለመሰወር ሲሞክሩ የተደረሰባቸው 426 ነጋዴዎች ተመሳሳይ ቅጣት በመጣሉ ችግሩ ከአምናው አንጻር መቀነሱን ጠቁመዋል፡፡

በጉጂ ዞን ባለፉት ስድስት ወራት 171 ሚሊዮን 800ሺህ ብር ገቢ መሰብሰቡንና  ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር  ከ24 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ እንዳለው ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም