ኢትዮጵያ ሰፊ የሰው ኃይልና የገበያ ዕድል የያዘች ምቹ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ናት - ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ቱሩዶ

107
አዲስ አበባ የካቲት 1/2012 (ኢዜአ)  ኢትዮጵያ ሰፊ የሰው ኃይልና የገበያ ዕድል የያዘች ምቹ የኢንቨስትመንት መዳረሻ አገር መሆኗን የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ቱሩዶ ተናገሩ። ኢትዮጵያ ሴቶችን ወደ አመራርነት በማምጣት ረገድ ተምሳሌት መሆኗንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨምረው ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ቱሩዶ ይህን ያሉት የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን አስመልክቶ ዛሬ ለአገር ውስጥና ለውጭ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በንግድ ዘርፍ  በጋራ መስራት የሚያስችላትን የመግባቢያ ስምምነት ከኢትዮጵያ የንግድ ቻምበርና የዘርፍ ማህበራት ጋር  መፈራረሟንም ይፋ አድርገዋል። ካናዳ በቀጣዩ ዓመት ከኢትዮጵያ ጋር በመተባባር ከከባቢ አየር ብክለት የጸዳ ቴክኖሎጂ ጉባዔን በአዲስ አበባ እንደምታስተናግድም ተናግረዋል። ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር ጊዜ ወስደው መወያየታቸውን ጠቅሰው፤ በቆይታቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምዕራፍ የሚያሸጋግሩ ታላላቅ ተግባራትን ማከናወናቸውን እንደተገነዘቡ ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የያዙትን ራዕይ እርሳቸውና አገራቸው እንደሚጋሩትም አውስተዋል። አገራቸው በአቅም ግንባታና በኢኮኖሚ መስክ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኗንም ጠቁመዋል። የኢትዮጵያን ምርጫ ቦርድ በመደገፍ አገሪቱ የዳበረ ዴሞክራሲ ለመገንባት የምታደርገውን ጥረት እንደሚያግዙም ገልጸዋል። በፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ ከሰለጠነ የሰው ኃይል እስከ ሰፊ የገበያ መዳረሻ የሚዘልቅ ዕድል ይዛለች ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ይህን ለመረዳት ሩቅ ሳይሄዱ አዲስ አበባን ብቻ መመልከት በቂ  ነው ሲሉ ነው ያብራሩት። ነገር ግን ለእያንዳንዱ ዜጋ ትክክለኛና እኩል የመስራት እድል ሳይመቻች ስለ ስኬት ማሰብ አይቻልም ነው ያሉት። በተለይ ሴቶች የትምህርትና የስራ ዕድል ከተመቻቸላቸው ማህበረሰብን በቀላሉ ከፍ ያደርጋሉ ብለዋል። በዚህ ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በካቢኔያቸው የጾታ እኩልነትን በማረጋገጥ ኢትዮጵያን በጉዳዩ መሪ አገር እንድትሆን ማስቻላቸውንም አንስተዋል።       ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ቱሩዶ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ለአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ የመጡ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት መሪዎች ጋርም ተወያይተዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም