ችግሮቻችንን በራሳችን መፍታት የምንችለው በአንድ ዓላማ በአንድ ልብ ስንሰራ ነው - የአፍሪካ ኅብረት

66
አዲስ አበባ የካቲት 1/2012 (ኢዜአ) 33ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ዛሬ ሲጀመር ሊቀመንበሩ የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል። በአሁኑ ወቅት አፍሪካዊያን በጋራ ሆነን ልንፈታቸው የሚገቡ በርካታ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ችግሮች መኖራቸውን ተናግረዋል። በተለይም በምስራቅ አፍሪካ ሠላምን የማረጋገጥ፣ አሸባሪነትን የመዋጋት እንዲሁም ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዘው የሚመጡ የጎርፍና ድርቅ አደጋዎችን ጠቅሰዋል። ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ ማላዊ፣ ዚምባብዌና ኢትዮጵያን የጠቀሱ ሲሆን በፖለቲካ ደግሞ የሊቢያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳንና ሶማሊያን ጉዳዮች አንስተዋል። በተለይ በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና በየጊዜው የሚፈጠሩ ፖለቲካዊ አለመረጋጋቶችን ተከትሎ ሴቶችና ህፃናትን ጨምሮ በርካታ ወጣቶች አሁንም ለስደት እየተዳረጉ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ይህንንም የኅብረቱ አባል አገራት በጋራ በመሆን ሊያስቆሙ እንደሚገባ አሳስበዋል። በተለይም ሠላምን የማስፈን፣ አሸባሪነትን የመዋጋትና መንግስታትን እንደገና የማቋቋም ስራ ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው ነው ብለዋል። አሁን ባለው ሁኔታ በሱዳን፣ በደቡብ ሱዳንና በሶማሊያ የነበሩ ችግሮችን ከመፍታትና አንፃራዊ ሠላም ከማስፈን አኳያ ጥሩ ለውጥ እየታየ መሆኑን የገለፁት ሊቀመንበሩ በቀጣይም በጋራ ልንሰራ ይገባል ብለዋል። በአህጉሪቱ ምርጫ የሚያካሂዱ በርካታ አገራት መኖራቸውን ጠቅሰው የምርጫ ተቋማትን የማዘመንና ትክክለኛ ምርጫ በማካሄድ ለአህጉሪቱ ሠላም ሁላችንም የድርሻችንን መወጣት ይገባል ሲሉም ተደምጠዋል። በተጨማሪም የሴቶችን የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የማህበራዊ ጉዳዮች ተሳትፎ የማሳደግ፣ በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ማስቆም ትልቅ ጉዳያችን ነው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል። የወጣቶች ስራ ፈጠራና ዘላቂ ሠላም የማስፈን ተግባራትም ትኩረት የምንሰጣቸው ቀዳሚ ስራዎቻችን ናቸው ብለዋል። ከዚህ ባሻገር በኅብረቱ አባላት መካከል የነፃ ገበያ ስምምነትን ተፈፃሚ ማድረግ፣ የአየር ትራንስፖርት ትስስርን ማጠናከር፣ የጋራ የመሰረተ ልማት አውታሮችን ማስፋፋት አስፈላጊ መሆኑንም አንስተዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም