የአፍሪካ አህጉር የልማት ፋይናንስ እርዳታን አማራጭ ከማድረግ ይልቅ ሌሎች አማራጮችን መፈለግ እንዳለበት ተጠቆመ

61
አዲስ አበባ ኢዜአ ጥር 30/2012  የአፍሪካ አህጉር የልማት እርዳታን የመጨረሻ አማራጭ ከማድረግ ይልቅ ከበለጸጉና አለም ዓቀፍ ድርጅቶች ጋር አጋርነትን ማጠናከር እንደሚገባ የአፍሪካ ልማት አዲስ አጋርነት (ኔፓድ) ሊቀመንበር ተናገሩ። 37ኛው የኔፓድ የመሪዎች ስብሰባ ዛሬ ተካሂዷል ። የኔፓድ ሊቀመንበር የሆኑት የሴኔጋል ፕሬዚዳንት ማኪ ሳል በመክፈቻው ወቅት ዘላቂና አካታች ልማት፣ ጠንካራ ማህበረሰብና የስራ እድል አለመኖር በአህጉሩ እያጋጠሙ ተግዳሮቶች መሆናቸውን ዘርዝረዋል። ''በመሆኑም አፍሪካን የበለጸገና ለዜጎቿ ምቹ የሆነች ለማድረግ በመተባበር መስራት ይኖርብናል'' ብለዋል። ለዚህም ከአለም አቀፍ ድርጅቶችና መንግስታት የሚገኝ የልማት ፋይናንስ እርዳታን የመጨረሻ ፋይናንስ ምንጭ አድርጎ ማየት ማብቃት እንዳለበት አስገንዝበዋል። ይልቁንም በአፍሪካ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጭ በመጠቀም የአህጉሪቱን የኢኮኖሚ ሽግግር እውን ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል። ''አገሮች ያላቸውን የተፈጥሮ ሃብት በመጠቀም በአህጉሪቱ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዘውን ወጣት አምራች ሃይል መጠቀም ይኖርባቸዋል'' ብለዋል። እርዳታን ከመጠበቅ ይልቅ የአለም አቀፍ ድርጅቶች ትብብርን ለማጠናከር የሚያስችል ጥረት ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ አመልክተዋል። በተለይም የግሉን ዘርፍ ኢንቨስትመንትን መሳብ፣ ስጋትን መቀነስ፣ የገንዘብ አቅርቦትን መጨመር፣ የተቀረጹ ፕሮጀክቶችን መተግበርና ሌሎችን ለማሳካት መሰራት እንዳለበት ገልጸዋል። ሊቀመንበሩ አፍሪካ በማህበራዊና ምጣኔ ሃብት ዘርፍ ማሻሻያዎችን ለማምጣት ትኩረት ማድረግ እንደሚገባም ጠቅሰዋል። ''በአህጉሪቱ ተንሰራፍቶ የሚገኘው የማህበራዊ ኢ-ፍትሃዊነትን በመፍታትና የኢንዱስትሪ ማስፋፋት ዕቅድን በማሳካት ለወጣቶች የስራ እድል መፍጠር ይኖርብናል'' ብለዋል። አለም አቀፉ የግብርና ልማት ድርጅት (ኢፋድ) ፕሬዚዳንት ጅልበርት ሆውንግቦ በበኩላቸው ''በአየር ንብረት ለውጥ የገጠር ማህበረሰብ ላይ ትኩረት ያደረገ አዲስ የፋይናንስ መርሃ ግብር ኢፋድ እያዘጋጀ ነው'' ብለዋል። እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፤ 15 በመቶ የሚሆነው የኢፋድ ትኩረት አፍሪካ አገሮች ላይ ነው። በመሆኑም ኢፋድ በአፍሪካ ገጠር ድህነትና ረሃብን ለመቀነስ የሚሰራ ሲሆን ከኔፓድ ጋር ያለውን አጋርነትርም እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም