ብሔራዊ የሚጥል ሕመም ሳምንት በኢትዮጵያ ለ5ኛ ጊዜ ይከበራል

66
ጥር 29/2012 (ኢዜአ)ብሔራዊ የሚጥል ሕመም ሳምንት ከመጪው የካቲት 1 ቀን ጀምሮ በኢትዮጵያ ለአምስተኛ ጊዜ ይከበራል። ኬርኤፕለፕሲ ከጤና ሚኒስቴርና ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር "እኔም የሚጥል ሕመም ይመለከተኛል"በሚል መሪ ሃሳብ የሚጥል ህመም ሳምንትን ለአምስተኛ ጊዜ ያከብራል። በዓለም ላይ 65 ሚሊዮን የሚሆን ሕዝብ በዚህ ህመም እንደሚጠቃ ጥናቶች ያሳያሉ። በኢትዮጵያ በዘርፉ በቂ ጥናት ባይደረግም ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በህመሙ እንደተያዙ ይገመታል ሲሉ የኬር ኤፕለፕሲ መስራች ወይዘሮ እናት የውነቱ ተናግረዋል። ከእነዚህ መካከል ወደ ህክምና ተቋማት የሚሄዱት ከ5 በመቶ አይበልጡም፤ 95 በመቶ የሚሆኑት ህሙማንም የህክምና ክትትል አያደርጉም። ማህበረሰቡ ህመሙን ከእርኩስ መንፈስ፣ ከፈጣሪ ቁጣና ከተለያዩ ነገሮች ጋር በማያያዝ ታማሚዎችን ወደ ህክምና ተቋም አይወስድም። እንደ ወይዘሮ እናት ገለጻ የዝግጅቱ ዓላማ ስለ ህመሙ ያለውን የተሳሳተ አመለካከት ለመቀየርና ግንዛቤ ለመፍጠር ነው። የተሳሳተው ግንዛቤ ተወግዶ የህመሙ ተጠቂዎች ሰብዓዊና ህገ መንግስታዊ መብታቸው እንዲጠበቅና ለአገራቸው ልማት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ለማድረግም እንዲሁ። በተጨማሪም የህብረተሰቡን ሰፊ የግንዛቤ ክፍተት መቀነስ እንዲቻል መንግስት ለሚጥል ህመም ትኩረት ሰጥቶ እንዲንቀሳቀስ ለማድረግ እንደሆነም ገልጸዋል። ድርጅቱ በተቋቋመበት አጭር ጊዜ በርካታ ስራዎችን መስራቱንና ለታማሚዎች የህክምና እድል ከማመቻቸት ጀምሮ መድሀኒት እንዲያገኙ፣ የስነ ልቦና ድጋፍ በመስጠትና በአነስተኛ የኑሮ ደረጃ የሚኖሩ ሴቶችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ለመፍታት በገቢ ማስገኛ ስራዎች ማሰማራቱን ጠቅሰዋል። ጉዳዩ የሚመለከታቸው የጤና መስኮች ላይ ተጽእኖ በማድረግም ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጠው እየሰሩ መሆኑንም ጠቅሰዋል። የሚጥል ህመም ተፈጥሯዊ በሆነ የአዕምሮ እክል፣ በጭንቅላት ላይ በሚደርስ አደጋ፣ በድንገተኛ ራስን መሳት፣ በተራዘመና በአስቸጋሪ ምጥ ወቅት በሚያጋጥም የኦክስጅን እጥረት ይከሰታል። በተጨማሪም የአልኮል መጠጦችና አደንዛዥ እጾችም የህመሙ መንስኤዎች ይሆናሉ። 'መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት አልሰጠውም' ያሉት ኃላፊዋ በቀጣይ ከጤና ሴክተሮች ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት ችግሩን ለመፍታት እንደሚሰሩም አውስተዋል። ኬርኤፕለፕሲ ኢትዮጵያ ከተባባሪ አካላት ጋር ባዘጋጀው ፕሮግራም ሳምንቱ ከየካቲት 1 እስከ 8 ቀን 2012 ዓ.ም በውይይት፣ በጤና ባለሙያዎች ስልጠና፣ በጎዳና ላይ ትምህርትና በእግር ጉዞ እንደሚከበር ገልጸዋል። ኬርኤፕለፕሲ በኢትዮጵያ ከተቋቋመ አራት ዓመታትን ያስቆጠረ ግብረሰናይ ድርጅት ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም